“የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊያን እህትና ወንድሞቹ ጋር ተሳስቦ እና ተባብሮ መኖር ያውቅበታል” አቶ ጣሂር መሐመድ

34

ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ)15ኛው የአማራ ክልል ባሕልና ኪነ ጥበባት ፌስቲቫል የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው። በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ጣሂር መሐመድ የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ጸንቶ፣ ባሕልና እሴቱንም በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ የሚያንጸባረቅ ሕዝብ ነው ብለዋል። “የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊያን እህትና ወንድሞቹ ጋር ተሳስቦ እና ተባብሮ መኖር ያውቅበታል” ሲሉም ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኹኔታዎች የአማራን ሕዝብ ያለስሙ ስም የሚሰጡ፤ ያለ ግብሩም የሚፈርጁ እንቅስቃሴዎች ይስተዋሉ እንደነበር አቶ ጣሂር አንስተዋል። በተለይም ላለፉት 50 ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የተሳሳተ ትርክት የሚሠሩ አካላት ስለነበሩ ሕዝቡን የማይገልጹ ምልከታዎች ተሰጥተውት ነበር ብለዋል። በዚህ ምክንያት በሕዝቦች ላይ ይደርሱ የነበሩ ችግሮችን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅረፍ ባሕል እና ኪነ ጥበብን ይዞ የአማራን ሕዝብ እውነቶች በትክክል ማሳየት ወሳኝ ስለመኾኑም አቶ ጣሂር ተናግረዋል።

አማራ ክልል ሀገርን ጭምር የሚያስጠሩ ታላላቅ የኪነ ጥበብ ሰዎች መፍለቂያ እንደኾነም በንግግራቸው አንስተዋል። በክልሉ የሚገኙ የባሕል ቡድኖች፣ አምባሳደሮች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በአማራ ሕዝብ ላይ የተሰጠውን የተሳሳተ ምልከታ ለማረም በጋራ መሥራት እንዳለባቸውም መልእክት አስተላልፈዋል።

የአማራ ሕዝብ ከሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጋር በወንድምና እህትነት፣ መልካም ወዳጅ እና ጎረቤት ኾኖ በአንድነት እና በመተሳሰብ የሚኖር ነው ብለዋል አቶ ጣሂር። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ይህንን እውነት በሥራዎቻቸው ሁሉ ማሳየት እንዳለባቸውም አቶ ጣሂር አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ባሕልን ለመዝናናት ብቻ ሳይኾን ያጋጠመንን ችግር ለመፍታት መሳሪያ አድርገን መጠቀም አለብን” ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)
Next article“የልማት እቅዶችን ዳር ለማድረስ በተደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ተመዝግበዋል!” ዶክተር ይልቃል አፋለ