“ባሕልን ለመዝናናት ብቻ ሳይኾን ያጋጠመንን ችግር ለመፍታት መሳሪያ አድርገን መጠቀም አለብን” ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)

37

ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ)15ኛው የአማራ ክልል ባሕልና ኪነ ጥበባት ፌስቲቫል የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ርእሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

የጥበብ መፍለቂያ፣ የድንቅ ባሕል መገኛ፣ የጀግንነት፣ የብልሃት፣ የመልካምነት እና የአኩሪ ታሪክ ባለቤት ነው፡፡ ዘመናትን የተሻገሩ ድንቅ ባሕሎች፣ ሀገር የጸናባቸው፣ ትውልድ ከትውልድ ጋር የተሳሰረባቸው ውብ እሴቶች፣ ታሪክ በደማቅ ቀለም የጸፋቸው አኩሪ ታሪኮች መገኛም ነው የአማራ ክልል፡፡

ከዘመን ዘመን የማይቋረጥ ጥበብ ይፈልቅበታል፣ ትውልድም ከጥበቡ እየቀዳ ጥሙን ያረካበታል፣ ማንነት የሚገለጥባቸው፣ ቀደምትነት የሚመሰከርባቸው፣ ነጻነት የሚነገርባቸው ድንቅ ባሕሎች ነበሩት፣ አሉት፣ ይኖሩታል፡፡ ለባሕሉ፣ ለታሪኩ፣ ለነጻነቱ እና ለማንነቱ ክብር አለው፡፡ ለሀገሩ እኔ ልቅደም ብሎ ይቀድማል፣ እርሱ ወድቆ ሀገሩን ያቆማል ጀግና እና ብልህ ሕዝብ ነው፡፡

ለዘመናት ጠብቋቸው፣ ደምቆባቸው የኖሩ ባሕሎቹን እና ጥበቦችን ዓለም ሁሉ ያይለት፣ አይቶም ይደነቅበት ዘንድ እንካችሁ ብሏል፡፡ ከአባት እና እናት የወረሰውን በምንም በማንም ያልተበረዘውን እንደ ጸና የኖረውን ባሕሉን፣ ጥበቡን፣ ታሪኩን እና እሴቱን ነው ያሳየው፡፡

በበፌስቲቫሉ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) እንዲህ አምረን በማክበራችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡ ባሕልና ኪነ ጥበብ ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የማይሰራው፣ የማይቀሰቅሰው እና የማያነሳሰው የለም ነው ያሉት፡፡

ሰው በባሕሉ፣ በአኗኗሩ በቁሳዊ ብቻ ሳይኾን በመንፈሳዊ ምግብ መኖር አለበት ብለዋል፡፡ ቁሳዊ ሃብት ብቻውን የሰውን ልጅ ዓለማዊ ኑሮ ሙሉ አያደርግም፣ የመንፈስ ምግብ ያስፈልጋል፣ የዓለማዊ የመንፈስ ምግብ ደግሞ ባሕልና ኪነ ጥበብ ነው ብለዋል፡፡ ባሕልና ኪነ ጥበብ መገነጢሳዊ ኃይል ስላለው ሰውን ያሰባስባል፣ ወኔ ያላብሳል፣ ያበረታታል ነው ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ፡፡ ባሕልና ኪነ ጥበብ በሰው ልጅ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሕይወት ያለው ሚና ታላቅ መኾኑን ገልጸዋል፡፡

ባሕልና ኪነ ጥበብ አዲስ አስተሳሰብ እንደሚያንጽ እና እንደሚያሳይም ተናግረዋል፡፡ ባሕልና ኪነጥበብን ትቶ መልማት፣ መማር እና እሴት ማስቀጠል እንደማይታሰብም ገልጸዋል፡፡ ለባሕልና ኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተሻለ ዘመን እየመጣ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላላቅ ስም ያላቸው በባሕልና በኪነ ጥበብ ታላቅ ሥራ የሠሩ ናቸውም ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ባሕልና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ባሕልን ለማሳደግ፣ እሴትን ለማስጠበቅ፣ ወጣቱን ለማስተማር፣ ባሕሉን እንዲያፈቅርና ሀገር ወዳድ እንዲኾን አስተዋጽዖ ሲያደርግ ቆይቷል፣ እያደረገም ነው፣ወደፊትም ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

ከዓመታት በኋላ የተካሄደው ባሕልና ፌስቲቫል ዓላማው ባሕላችን ለሰላም እና ለአንድነታችን ነውም ብለዋል፡፡ ክልሉ ውስጣዊ ሕመም አለበት ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሕመሙን መፈወስ አለብን፣ ሕመሙን ለመፈወስ ደግሞ ሚናውን የሚጫወተው ባሕል መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ይልቃል በባሕላችን የችግር አፈታት ስልት ምንድን ነው፣ አንድነቱን እንዴት ያጠናክራል የሚለውን ማየት ላጋጠመው ችግር መሳሪያ ኾኖ ያገለግላል ነው ያሉት፡፡ ባሕልን ለመዝናናት ብቻ ሳይኾን ያገጠምን ችግር ለመፍታት መሳሪያ አድርገን መጠቀም አለበንም ብለዋል፡፡

ችግር የሚፈቱ፣ ግጭት የሚያስወግዱ ባሕላዊ ተቋማት መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተቋማት መኖራቸውን አንስተዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡

የገጠመንን ችግር ለማስወገድ ባሕል አንዱ መሳሪያ ስለኾነ መንግሥት ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ አማራ ክልል የሚያማልሉ ባሕሎች ያሉበት ክልል መኾናቸውን አንስተዋል፡፡ አንድነት የሚታይበትን ባሕል ማጠናከር አለብንም ብለዋል፡፡ በየደረጃው ያለው ባሕልና ቱሪዝም አጠናክሮ መሥራት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

ባሕል የሚያከብርና የሚያስከብር መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ልዩ የኾነውን ባሕል አውጥቶ ማሳየት፣ ማጽናት እና ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ወጣቶች በሙያው ገብተው ሕዝባቸውን የሚያገለግሉ መኾን እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡ ባሕል የትናንት ማንነትን እና መምጫ መንገድን የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ባሕላችንን ጠብቀን መጓዝ ይገባናል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ፡፡ የባሕልና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

ፌስቲቫሉ እንዲሳካ ላደረጉ፣ ባሕላቸውን ላስተዋወቁ ሁሉ ርእሰ መሥተዳድሩ አመሥግነዋል፡፡ ወጣቶች ባሕላቸውን እንዲጠብቁና እንዲያስተዋውቁም አደራ ብለዋል፡፡ ባሕል የሚጎላውና እና የሚያድገው በመጠበቅ መኾኑን አመላክተዋል፡፡ ባሕልና ኪነ ጥበቡን እንደግፍ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ባሕልና ኪነ ጥበብ ለክልሉ ሰላምና አንድነት ታላቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ክልል የጥበብ ጓዳ፣ የታሪክ አምባ፣ የቅርስ ማኅደር፣ የብዝኃነት ተምሳሌት ነው” አየለ አናውጤ (ዶ.ር)
Next article“የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያዊያን እህትና ወንድሞቹ ጋር ተሳስቦ እና ተባብሮ መኖር ያውቅበታል” አቶ ጣሂር መሐመድ