“የአማራ ክልል የጥበብ ጓዳ፣ የታሪክ አምባ፣ የቅርስ ማኅደር፣ የብዝኃነት ተምሳሌት ነው” አየለ አናውጤ (ዶ.ር)

48

ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ)15ኛው የአማራ ክልል ባሕልና ኪነ ጥበባት ፌስቲቫል የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) በተገኙበት እየተከናወነ ነው፡፡

በማጠቃላያ ዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) የአማራ ሕዝብ ታሪክ በሀገረ መንግሥት ምስረታ፣ በአሥተዳደር እና ጽንሰ ሃሰባም ኾነ ገቢራዊነት፣ በአርበኝነት እና በሀገር ሉዓላዊነት የቀደመ መረዳት ያለው ነው ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል የጥበብ ጓዳ፣ የታሪክ አምባ፣ የቅርስ ማኅደር፣ የብዝኃነት ተምሳሌት ነው፡፡ በክልሉ በአራቱም ማዕዛናት ጥበብን ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ወርሳናል ነው ያሉት፡፡

የላሊበላን ኪነ ሕንጻ፣ የፋሲል ግንብ እና ሌሎች የማንዘነጋቸውና የወረስናቸው የጥበብ አሻራዎች ናቸው ብለዋል፡፡

ቀለም ነክረው፣ ቆዳ ፍቀው፣ ዕውቀቶችን በብራና ጽፈው እና ሰንደው፣ ታሪክን በቀለም ጠብታ ጽፈው ለዛሬ ያቆዩልን አባቶቻችን ሌላኛው የጥበብ ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡ የሽምግልና የግጭት አፈታት ሂደቶችም የክልሉ ባሕላዊ እሴቶች ናቸው ብለዋል፤ እነዚህ እሴቶቻችን ዝቅ ሲል የአብሮነት አምዶች፣ ከፍ ሲል የብሔራዊ አንድነት እና መግባባት መድኃኒቶች መኾናቸውንም አንሰተዋል፡፡

እነዚህ ውብ ባሕሎች በማኅበረሰብ ትስስር የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡ በተለይም አሁን ላለው የሰላም መደፍረስ እና ኢተገማች ለኾነው የሰላምና ደኀንነት ስጋቶች አይነተኛ ሚና የሚወጡ በመኾናቸው ድጋፍ ሊደረግባቸው እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የአራቱ የሙዚቃ ቅኝቶች መፍለቂያ፣ አንጋፋ ጥበበኞችን ያፈራ ማኅጸነ ለምለም ሕዝብ ነውም ብለዋል፡፡ በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ፣ ሀገር ስትደፈር የጦር አዝማች የኾነ አይተኬ ሚና ያለው ሕዝብ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በክልሉ ውብ የኾኑ አያሌ ባሕላዊ ሃብቶች አሉ ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው እነዚህን ውብ ሀብቶች ማስተዋወቅ ከሁሉም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

ባሕላችንን ካስተዋወቅን ማንነታችን ይከበራል፤ አንድነታችን ይጠነክራልም ብለዋል፡፡ በመንግሥት በኩል ለዘርፉ የሚገባውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የተጠናከረበት፣ አንድነት የታየበት እንደኾነም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article15ኛው የአማራ ክልል ባሕልና ኪነ ጥበባት ፌስቲቫል የመዝጊያ ዝግጅት በባሕርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
Next article“ባሕልን ለመዝናናት ብቻ ሳይኾን ያጋጠመንን ችግር ለመፍታት መሳሪያ አድርገን መጠቀም አለብን” ርእሰ መሥተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር)