
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ መንግሥት ድንበሩን ክፍቶ አድርጎ ባደረገልን መልካም አቀባበል ከችግርና ከሞት ታድጎናል” ሲሉ በሱዳን ግጭት ተሰደው በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ የተጠለሉ ሱዳናዊያን ስደተኞች ገለጹ።
ስደተኞቹ እንደገለጹት በኢትዮጵያ የተደረገላቸው አቀባበልና ድጋፍ በስደት ወቅት ሊደርስባቸው ከሚችል እንግልትና ስቃይ ታድጓቸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት አብዱልከሪም ሙሃመድ እንዳለው በሱዳን በተከሰተ ግጭት ምክንያት ከሀገሩ ተሰዶ ላለፉት ሦስት ወራት በመተማ ዮሐንስ መጠለያ ጣቢያ እያሳለፈ ይገኛል።
እሱን ጨምሮ በርካታ ስደተኞች ወደ መተማ ሲገቡ በኢትዮጵያ መንግሥት መልካም አቀባበልና ድጋፍ እንደተደረገላቸው ጠቅሶ ለእዚህም ያለውን ምስጋና ገልጿል።
ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ቀን ጀምሮ ምግብ፣ የመጠጥ ውኃና መጠለያ እያገኙ መኾናቸውን ጠቅሶ፣ አንዳንዴ የሚስተዋለው የምግብና የመድኃኒት እጥረት እንዲስተካከል ጠይቋል።
“ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ትልቅ አክብሮትና ምሥጋና አለኝ” ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ ሱዳናዊ ተፈናቃይ አሚራ ሙሃመድ ናቸው።
ኢትዮጵያ ድንበሯን ለስደተኞች ክፍት አድርጋ መቀበሏ በተለይ በስደት ወቅት በሴቶችና ህጻናት ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ ችግርና ሞት ማስቀረቱን ተናግረዋል።
በሱዳን በተፈጠረ ግጭት ከ13 የቤተሰብ አባላት ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጡ ገልጸው፣ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በፍቅር እንደተቀበሏቸው ተናግረዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ በመጠለያው በቆዩባቸው ጊዜያት የምግብና የውኃ ድጋፍ እያገኙ ቢሆንም ለህጻናት ልዩ እንክብካቤ በማድረግ በኩል የተወሰኑ ክፍተቶች አሉ።
በተለይ ለህጻናት የሚኾን የአልሚ ምግብ ድጋፍ እንዲደረግላቸው የጠየቁት ተፈናቃዩዋ፣ “በአካባቢው ስደተኞች በነጻነት መንቀሳቀስ የምንችልበት ኹኔታ ሊመቻችልን ይገባል” ብለዋል።
ሌላኛው ስደተኛ አቶ አብዱላዚዝ ሀሰን እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ያደረጉልን አቀባበል የባዕድነት ስሜት እንዳይሰማን አድርጓል።
“በስደት መጥተን የተደረገልን ወንድማዊ አቀባበል በሀገሬ ያለው ያህል እንዲሰማኝ አድርጓል፤ ለእዚህም ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ምሥጋናዬ ከፍ ያለ ነው” ያሉት አቶ አብዱላዚዝ፣ በመተማ መጠለያ ጣቢያ ምግብ፣ ውኃና ማረፊያ ከማቅረብ ጀምሮ የጤና ምርመራ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በመጠለያው በኢትዮጵያ መንግሥትና በተለያዩ ለጋሽ አካላት የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የመተማና አካባቢው የስደተኞች ካምፕ አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ እንዳሉት፣ በሱዳን በተከሰተው ግጭት ከስምንት በላይ ሀገራት ዜጎች በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
ስደተኞቹ የምግብ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ፣ የጤናና መሰል አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል።
በቀጣይ ከተባበሩት መንግሥታትና ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በመኾን የስደተኞችን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት እንደሚሠራም ገልጸዋል።
አቶ ታምራት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገሮች ተሰደው የመጡ ተፈናቀዮች በመጠለያ ካምፖች እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።
በመተማና አካባቢውም እስካሁን ድረስ የተጠለሉ ስደተኞች ከ15 ሺህ በላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናገድ በኩል ኢትዮጵያ ለሌሎች ትምህርት የሚኾን የቆየ ልምድ እንዳላት ያስታወሱት አስተባባሪው፣ በችግር ውስጥም ስደተኞችን ተቀብላ እያስተናገደች መኾኗን ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!