በባሕር ዳር ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡

328

በባሕር ዳር ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር ዋለ፡፡

በባሕር ዳር ከተማ ዳግማዊ ዓፄ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ ‹ሰማዕታት› አካባቢ አንድ ግለሰብ ተከራይቶት ከነበረ መኖሪያ ቤት በኅብረተሰቡ በተሰጠ ጥቆማ 449 ሽጉጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የኮሙዩኒኬሽንና ሚዲያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ኮማደር መሠረት ደባልቄ ለአብመድ እንዳስታወቁት የባሕር ዳር አድማ ብተና ፖሊስ ከ5ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ ጋር በቅንጅት በፈፀሙት ሕገ ወጥ ድርጊትን የመቆጣጠር ተግባር ሕገ ወጥ ሽጉጦቹ ተይዘዋል፡፡ ጉዳዩን ከምንጩ ለማረጋገጥ የምርመራ ቡድን እንደተቋቋመም አስታውቀዋል፡፡

ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያውን እንዳከማቸው የተጠረጠረው ግለሰብ ለጊዜው በቁጥጥር ስር አለመዋሉን ያስታወቁት ኮማንደር መሠረት የቤቱ አከራይ ግን በቁጥጥ ስር እንደዋሉና ያከራዩትን ሰው ማንነት እንደማያውቁ መግለጻቸውን አመልክተዋል፡፡

ግለሰቡ በቤቱ ተከራይቶ መኖር ከጀመረ ወር እንዳልሞላው ያስታወቁት ኮማንደር መሠረት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያውን በአይሱዙ ጭኖ እንዳመጣው ተጠቁሞ እንደተያዘና በርካታ ቁጥር ያለው የባጃጅ ጎማም ከነመዳሪ አብሮ ተከማችቶ መገኘቱንም ገልጸዋል፡፡

ግለሰቦች ቤታቸውን የሚያከራዩትን ሰው ማንነት በትክክል ማወቅና መታወቂያ ኮፒ አድርገው የመያዝ ኃላፊነት እንዳለባቸው የገለጹት ኮማደር መሠረት ኅብረተሰቡ ላደረሰው ጥቆማም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- አብርሃም በዕውቀት

Previous articleከደሳሳ ጎጆ እስከ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ምንጭነት።
Next articleበአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በጓጉሳ ሽጉዳድ ወረዳ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ13 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡