
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 06/2012ዓ.ም (አብመድ) ባለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን የሕትመት ብዙኃን መገናኛ ዘርፉን ከተቀላቀሉ ክልላዊ ተቋማት መካከል የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ቀዳሚውና አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ በአዋጅ ቁጥር 56/1993 ከመቋቋሙ ቀድም ብሎ ነበር በሕትመት ዘርፉ ወደ አንባብያ መድረስ የጀመረው፡፡
በአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ታሪክ ቀዳሚውን ቦታ የምትይዘው በየሳምንቱ እየታተመች ለንባብ የምትበቃው የበኩር ጋዜጣ ናት፡፡ በኩር የሚለው መጠሪያዋ የግዕዝ ቃል ነው፤ትርጉሙም የመጀመሪያ ወይም ቀዳሚ ማለት ነው፡፡
ጋዜጣዋ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕትመት የበቃችው ሐምሌ 19/1986 ዓ.ም ነበር፡፡ በመጀመሪያ እትሟም 10 ቅጂዎችን ለአንባቢዎቿ አድርሳ እንደነበር በወቅቱ የበኩር ጋዜጣ ዘጋቢ የነበሩት ጋዜጠኛና ደራሲ አበረ አዳሙ አስረድተዋል፡፡ ጋዜጣዋ ባለ ጥቁርና ነጭ ቀለም ሆና ስምንት የገጽ ብዛት ነበራት፡፡
ጋዜጣዋ በቋሚነት እየታተመች ለደንበኞች መድረስ የጀመረችው ግን ታኅሳስ 7 ቀን 1987 ዓ.ም ሳምንታዊ የሐሙስ ጋዜጣ ሆና ነበር፡፡ የዜና ገፅ፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ኢኮኖሚያዊ ልማት፣ ባሕልና ስፖርት የሚሉ አምስት ዓምዶች ደግሞ አካትታ ትይዝ ነበር፡፡ የተነባቢነት ደረጃዋና ተወዳጅነቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የነበር ቢሆንም የሕትመት መጠኗ ግን አራት ሺህ ቅጅ ብቻ ሆኖ በርካታ ዓመታትን እንዳሳለፈች መሥራች ጋዜጠኞች ያስታውሳሉ፡፡
ጋዜጣዋ የደንበኞቿን የንባብ ጥማት ለማርካትና አዳዲስ መረጃዎችን ለማድረስ ያነገበችው ዓላማ እንዲሳካ ትታትርም ነበር፡፡ ለዚህ በወቅቱ የነበሩ ጋዜጠኞች ድርሻ ከፍተኛ ነበር፡፡ በተለይ በወቅቱ የነበረው የቴክኖሎጅ ውስንነትና አቅርቦት አለመሟላት ለዘጋቢዎች ትልቅ ፈተና እንደነበር ይነገራል፡፡ በጋዜጣዋ ሕትመት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የተሟላ ቴክኖሎጅ አቅርቦት ባለመኖሩ ጋዜጠኞች አብዛኛውን ሰዓታቸውን ይወስዱት የነበረው ለጉልበት ሥራ ነበር፡፡ ሕትመቶች ተጠናቅቀው ወደ አንባብያን ይደርሱ የነበሩት በጋዜጠኞች አዎንታዊ ተነሳሽነት ነበር፡፡
በወቅቱ ለጋዜጣዋ ሥራ አገልግሎት ይሰጥ የነበረው አንድ ኮምፒውተር ብቻ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ የኮምፒዩተር ጽሕፈት የሚችል ሰው ጠፍቶ ጸሐፊ ከአዲስ አበባ እስከማስመጣት ተደርሶ እንደነበር ጋዜጠኛ አባትሁን ዘገየ አስታውሰዋል፡፡
የጽሑፍ ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላ የነበረው ሂደት ሌላኛው በወቅቱ የነበሩ ጋዜጠኞች ፈተና ነበር፡፡ የጹሑፍ ሥራው እንደተጠናቀቀ በወረቀት ከታታመ በኋላ የገጹ ንድፍ፣ ቅርፅና ቅንብር ሥራውን ለማከናወን ምላጭ፣ ብርሃን አስተላላፊ ቁስና ሌሎች ግብዓቶች ያስፈልጉ ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ ችግር ቀርቷል፡፡ ከሕትመት እስከ ማተሚያ ቤት የአላላክ ሂደት እጅግ ዘመናዊ በሆነ የመገናኛ ብዙኃን ቴክኖሎጅ የተደገፈ ሆኗል፡፡ ጋዜጠኞች ሙያዊ ኃላፊነታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩም ሆነዋል፡፡
በይዘት ስብጥርም ሆነ በገጽ ብዛት ከዓመት ዓመት ማሻሻልን እያሳየች ትገኛለች፡፡ ሕትመቷም የተሟላ ቀለም ሕትመት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ወቅትም በየሳምንቱ ሰኞ ለንባብ እየበቃች ትገኛለች፡፡ ሳምንታዊ የሕትመት መጠኗም ከ10 ሺህ ቅጂ በላይ ደርሷል፡፡
በበኩር ፈር ቀዳጅነት የተጀመረው የድርጅቱ የሕትመት ተደራሽነት ለክልሉና ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ ተደራሲያን አማራጭ የመረጃ ምንጭ ናቸው፡፡ በሦስቱም የብሔረሰብ ቋንቋዎች ማለትም ቺርቤዋ፣ በአዊኛ ፣ ኽምጠዊከ በኽምጣና እና ሂርኮ በኦሮሚኛ ጋዜጦች ለንባብ እየበቁ ይገኛሉ፡፡
ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ