
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሀገሬው ሰው አምላኩን ሲማጸን የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ አትንሳኝ፣ ጌታዬ ኾይ የሰው እጅ አታሳየኝ፣ በሰው ፊትም አታስገርፈኝ፣ ሰጪ እንጂ ተቀባይ አታደርገኝ፤ አቤቱ ጌታዬ በቁር የምጠጋባት፣ በሐሩር የምከለልባት፣ ገመናዬን የምሸፍንባት፣ ልጆች ወልጄ በበረከት ተመልቼ የምኖርባት ቤት አትንሳኝ፣ አታሳጣኝ ይላል፡፡ ቤት ገመና ከታች ናት እና፡፡ ሞቴንም በክረምት አታድርገው ይላል፡፡
ደመናው ሲከብድ፣ ዝናብ በቸርነቱ ሲወርድ፣ አፍላጋት ሞልተው ሲደነፉ፣ መብረቅ ከሰማይ ሲወነጨፍ ቤት ያለው ወደቤቱ ይገባል፣ የክረምቱን ወራት በቤቱ ያሳልፋል፡፡ “ዞሮ ዞሮ ከቤት፣ ኖሮ ኖሮ ከሞት” እንዲሉ ቀን ሲደክም የዋለው ወደ ቤቱ ይጓዛል፣ በቤቱም ተጠልሎ ጨለማውን ያሳልፋል፡፡ በቤቱም በገባ ጊዜ በሰላም አውሎ በሰላም የመለሰው አምላኩን ያመሠግናል፡፡
በክረምት እንኳን የሰው ልጅ አዋዕዋፋትም አስቀድመው ቤታቸውን ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ደጋግ ነብሶች ግን ቁር ባለበት፣ ዝናብ በበዛበት፣ ተራራዎች በጉም በተሸፈኑበት ክረምት ያለ ቤት ቀርተዋል፡፡ ሲደክማቸው የሚያርፉበት፣ ቤት ያፈራውን አምላካቸውን አመሠግነው የሚጎርሱበት፣ ከቁር የሚጠጉበት፣ ከሐሩር የሚጠለሉበት፣ ከዝናም የሚከለሉበት፣ ከልጆቻቸው ጋር ኾነው ደስታ የሚያዩበት፣ እንግዳ ጠርተው የሚያስተናግዱበት፣ የተቸገረን የሚረዱበት፣ ገመናቸውን የሚሸክፉበት ቤት የላቸውም፡፡ ወፍ ለልጇ ጎጆ ሠርታ ልጆቿን በምትሰበስብበት፣ የሰማይ አሞራ ልጆቿን ሰብስባ ወደ ዋሻ በምትገባበት በዚህ ምድሩም ሰማዩም ውኃ በኾነበት በክረምት እነዚህ ደጋግ ሰዎች ቤት አልባ ኾነዋል፡፡
የቤታቸው ጉልላት ፈርሶ፣ ሃብትና ንብረታቸው ተወርሶ የሰቀቀን ኑሮን መግፋት ከጀመሩ ጊዜያት ነጉደዋል፡፡ ሳይሰስቱ የሚሰጡት፣ ስሞት አፈር ስኾን እያሉ የሚያጎርሱት፣ የሰው እጅ ተመልካች ኾነዋል፡፡ በሚወዷት ሀገራቸው፣ በሚናፍቋት ቀያቸው፣ አያሌ ዓመታትን ባሳለፉባት ሥፍራቸው መቀመጫ አጥተው፣ እንደ በደለኛ ተቆጥረው የመከራ ጊዜያትን አሳልፈዋል፡፡ እነሆ ዛሬም የፈተናው ጊዜ አላለፈላቸውም፣ የመከራው ዘመን አልተቋጨላቸውም፡፡
ጌትዬ ደርቤ ይባላሉ፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ በሚገኝ መጠለያ ጣብያ ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው ከመጡ አንድ ዓመት ከስምንት ወራት አስቆጥረዋል፡፡ ከሞቀ ቤታቸው በግፍ ወጥተው፣ የችግር ጊዜያትን እያሳለፉ ነው፡፡ እሳቸውም የእርሳቸው አባትና እናት ተወልደው ያደጉት በማንነታቸው ውጡ በተባሉበት ምድር ነው፡፡ “እኔ ተወልጄ ያደኩት አያቶቼ ተወልደው ባደጉበት ነው ብለዋል፡፡ እኛ ለመንግሥት ታላቅ ግብር ከፋዮች ነን፣ ብዙ ንብረት ያለን ሰዎች ነበርን፣ ያ ሁሉ ነው ዛሬ ላይ እንዳልነበር የኾነው፣ እኛ የምናውቀውም የኖርንበትም የተወለድንበትን አካባቢ ነው፣ ስንፈናቀል ብቻ ነው ወደዚህ የመጣነው፣ ከፖለቲካ ውስጥ የለንበትም፣ ወንጀለኞችም አይደለንም፣ ከአለው ኅብረተሰብ ጋር ተጋብተን አብረን የምንኖር ነን፡፡ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ጋር ሳንስማማ ቀርተን አይደለም ከዚያ የወጣነው” ነው ያሉኝ፡፡
ተወልደው ካደጉበት ቀዬ ያስወጧቸው ሸኔ እና ተባበሪ ኀይሎች መኾናቸውንም ነግረውኛል፡፡ “ባለቤቴ ኦሮሞ ናት፡፡ አራት ልጆች የወለደችልኝ፡፡ እኔን እና ባለቤቴን አለያይተውናል፡፡ ልጆቼ በአማራ አባት ስለሚጠሩ እናንተ አታስፈልጉም ተብለው እኔ ልጆቼን ይዤ እንድወጣ ተደረኩኝ፡፡ ሚስቴ እዛው ቀረች፡፡ አሁን ሚስቴና ልጆቿ አይገናኙም፡፡ በአካል ቀርቶ በስልክም አይገናኙም፡፡ እኔ ስወጣ ባለቤቴ ነብሰ ጡር ነበረች፣ የወለደችውን ልጅ ወይ አንቀን እንገድለዋለን ወይም ወስደሽ ጫካ ካልጣልሽ እያሉ ቀንና ማታ ሲያሰቃዩዋት ነበር፣ ልጇን የወለደችው ቤቱን ጥላ ወጥታ በጫካ ውስጥ ዳስ ጥላ ነው፡፡ እስከዚህ ድረስ ነው ግፍ የተሰራብን፡፡ የግፉን ጥግ ማን እንደሚያፍሰው እግዚአብሔር ይወቀው፣ በእኛ ላይ የተሠራው ግፍ በጣም ከባድ ነው” ብለውኛል፡፡
ተወልደው ባደጉበት ሥፍራ ቦታቸው የሞላ፣ ትዳራቸውም ያመረ ነበር፡፡ አሁን ግን ያ ሁሉ የለም፡፡ “በመጠለያ ጣብያ ውስጥ መኖር ምንም የምታነሳለት በጎ ነገር የለውም፡፡ እርዳታ ወሩን ጠብቆ የሚሰጠን የለም፣ ሰው በረሃብ ነው ያለው፡፡ ሰዉ በመጠለያ ውስጥ ረጅም ጊዜ ከመኖሩ የተነሳ ተስፋ ወደ መቁረጥ እየሄደ ነው ” ይላሉ፡፡
ከረሃቡና ከችግሩ ሕይወት አልፎ በመጠለያ ውስጥ የኩፍኝ በሽታ ተነስቶ እንደነበርም ነግረውኛል፡፡ በሽታውን ለመቆጣጠር የሕክምና ባለሙያዎች ርብርብ ባያደርጉ ኖሮ ብዙ ሰው ይጎዳ ነበር፡፡ ያም ሆኖ አሁንም አሳሳቢ ነው ብለውኛል፡፡ “ ሁሉም የምግብ እጥረት ያለበት ነው፣ ጉዳተኛ ነው” ይላሉ ከረሃብ ላይ በሽታ ሲጨመርበት አደጋው የከፋ እንደኾነ ሲናገሩ፡፡
መንግሥትም ድጋፍ አድራጊ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም ሲያደርጉት የነበረውን ድጋፍ ቀንሰዋል ነው ያሉኝ፡፡
ጉዳት፣ ረሃብ፣ ችግር አለ፡፡ ሁነኛ መጠለያም የለም ብለውኛል፡፡ “በመጠለያ ውስጥ መኖር አስቸጋሪ ነው፡፡ ልጆች ያለቅሱብሃል፣ አዛውንቶች ሲንገላቱ ማየት፣ እድሜን ይቀንሳል፣ በሽተኛ ያደርጋል፣ ይሄ ነው ብሎ ለመናገር ከባድ ነው” ብለውኛል፡፡ እስከመቼ ድረስ ነው እንዲዚህ ኾነን የምንኖረው? ነው የሚሉት፤ ወደ ቀያችን እንዲመልሱን እንፈልጋለን፣ ሁሉም በቦታው ራሱን ችሎ ነው መኖር የሚፈልገው፣ ተረጂ ሆኖ መኖር የሚፈልግ የለም፣ ሁላችንም በአንድ መንግሥት ሥር የምንተዳደር ነን፣ ወደ ቀያችን መልሱን ብለን ጠይቀናል ነው ያሉኝ፡፡
መንግሥት ግን ዘላቂ የሆነ መፍትሔ እየሰጣቸው አለመኾኑንም ነግረውኛል፡፡ ወጣቶች ተስፋ እየቆረጡ ለስደት እየተዳረጉ፣ ሕፃናት ለጉልበት ብዝበዛ እየተጋለጡ ነውም ብለውኛል፡፡ ዘላቂ መፍትሔ እንሻለን፣ ዘላቂ መፍትሔው እስኪመጣ ድረስ ግን የዕለት ጉርስ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡ “ የምናርሰው መሬት ሳይኖር፣ የምንነግደው ንግድ በሌለበት፣ በመጠለያ ውስጥ እየኖርን ምግብ ካልቀረበልን እንዴት ነው የምንኖረው?” ይላሉ፡፡ ግብርን የምንከፍልበት መንግሥት የት ነው ያላችሁ ብሎ ጠይቆን አያውቅም፡፡ ብንሞትም ብንድንም በቀያችን ነው መኖር የምንፈልገው ነው ያሉኝ፡፡
በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር የሥነ ሕዝብ ባለሙያና በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለሚኖሩ ወገኖች አስተባበሪ አንተነህ ገብረ እግዚአብሔር በከተማዋ ከ30 ሺህ በላይ የሚኾኑ ወገኖች በመጠለያ እና በኅብረተሰቡ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ ነግረውኛል፡፡ ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙት በመጠለያ ጣብያ ውስጥ ለሚገኙ 26 ሺህ ወገኖች እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ ለተፈናቃይ ወገኖች የምግብ እጥረት እንዳለባቸውም ነግረውኛል፡፡
ለረጅም ጊዜ በከተማ ሲኖሩ በአካበቢው ማኅበረሰብ፣ በባለሃብቶች፣ በሃይማኖት ተቋማት እና በአንዳንድ በጎ አድራጊ ድርጅቶች እየታገዙ መቆየታቸውን ነው የገለጹት፡፡
በመንግሥት እየተደረገው ያለው ድጋፍ አጥጋቢ አይደለም ያሉት አስተባባሪው ድጋፍ ማድረግ ካልተቻለ የከፋ ችግር ላይ ሊወድቁ እንደሚችልም ነግረውኛል፡፡ ዋናው ችግር የምግብ ነውም ብለውኛል፡፡
ይመለሳሉ የተባለበት ጊዜ እየረዘመ መሄዱንም ገልጸዋል፡፡ የመመለሻ ጊዜው እየረዘመ ስለሄደ የተሻሉ መጠለያ ጣብያዎችን ከደብረ ብርሃን ወጣ ብሎ በምትገኝ ባቄሎ በተሰኘች ሥፍራ አሰርተው እያስጠለሉ መኾናቸውንም ነግረውኛል፡፡ ድጋፍ ማድረግ የሚሹም ወደ ባቄሎ መጠለያ ጣብያ እየሄዱ ማድረግ እንደሚችሉም አስታውቀዋል፡፡ የኩፍኝ በሽታውን ለመከላከል የጤና ባለሙያዎች በትኩረት እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ በመጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳያሬክተር ብርሃኑ ዘውዱ ተፈናቃይ ወገኖችን በመደገፍ በኩል ብዙ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ክፍተቱ የተፈጠረውም ካለው ችግር አንጻር ነው ብለዋል፡፡ በተቻለ መጠን ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ቅድሚያ እየሠጡ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ግን አነሰተኛ ነውም ብለዋል፡፡
በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም ገልጸዋል፡፡ ቢያንስ ከሌላ ቦታ ተፈናቅለው የመጡ ወገኖች የከፋ ችግር እንዳይገጥማቸው እና ረሃብ እንዳያጠቃቸው እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ ተፈናቃዮችን ከሌሎች ክልሎች ጋር በመነጋገር ወደ ቀያቸው ለመመለስ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ሰላሙን ማስቀጠል ከተቻለ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ ይቻላል ነው ያሉት፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን መሸከም የማይችል የትኛውም የኢትዮጵያ ግዛት መኖር የለበትም ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን በቂ መኾኗንም አስገንዝበዋል፡፡
በታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!