“ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ሩስያ ድጋፍ ታደርጋለች” በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር

31

ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት ሩስያ ትብብርና ድጋፍ እንደምታደርግ በኢትዮጵያ የሩስያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪን ገልጸዋል።

አምባሳደር ኢቭጌኒ ተርኪን የአየር ሁኔታ መለወጥ የውኃ ሃብትን በመቀነስ፣ በግብርና ምርት ላይ ጫና በማሳደርና ሌሎች ውስብስብ ችግሮች በመፍጠር ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩ ዓለም አቀፍ መሆኑን ገልጸዋል።

ችግሩ በአንድ አሕጉር ወይንም ቀጣና የሚወሰን ባለመሆኑ አለም አቀፍ ትብብርን በማጠናከር ተጽእኖውን መከላከል ያስፈልጋል ብለዋል።

አምባሳደሩ ኢትዮጵያ በዚህ ዙሪያ የምታደርገውን ጥረት አድንቀው፤ የአየር ንብረት ተጽዕኖን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት የሩስያ ትብብርና ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ያለውን ተግባር ሩስያ በምርምር ዘርፍ መደገፍ ትሻለችም ብለዋል።

ለዚህም ሁለቱ ሀገራት ላለፉት 30 አመታት በባዮሎጂካል የምርምር ዘርፍ በትብብር ሲያከናውኗቸው የቆዩ ተግባራትን ለማጠናከር እየሠሩ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ በቋሚነት የሚሰራ የባዮሎጂካል የምርምር ኢንስቲትዩት ለማቋቋም እቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል።

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ የዓለም ሙቀት በአማካይ በ1 ነጥብ 2 ድግሪ ሴንቲግሬድ እየጨመረ በመምጣቱ የጎርፍ አደጋ፣ ድርቅ፣ የዝናብ ስርጭትና መጠን መዛባት እንዲሁም የአካባቢ መራቆት እያስከተለ ይገኛል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት ለዓለም ለማስተዋወቅ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ላይ በትብብር መስራት ይገባል” የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሐምሌ 10 በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ በመትከል ታሪክ እንዲሠራ ጥሪ አቀረቡ።