“22 ሺህ 500 ለሚደርሱ የወንጀልና የፍታ ብሔር መዝገቦች ውሳኔ ተሰጥቷል” የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

49

ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የ2015 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም እየገመገሙ ነው። የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የ2015 በጀት ዓመት የ11 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ለሕግ፣ ፍትሕና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኘሬዚዳንት አብየ ካሳሁን የፍርድ ቤቶችን የ2015 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን አቅርበዋል።

በበጀት ዓመቱ በጦርነት ውስጥ በነበሩ የተወሰኑ ወረዳና ንዑስ ፍርድ ቤቶች አገልግሎት ሳይሰጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ከመንግሥትና ረጅ ድርጅቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በሰሜን ወሎና ዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጦርነትና በግጭት ውስጥ በቆዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የፍርድ ቤት ዳኞች ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ዳኞችንና ሰራተኞችን አቅም ለማጎልበት ስልጠና መሰጠቱንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ቴክኖሎጅዎችን በማስፋት የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ በኩልም ውስንነት መኖሩን አንስተዋል።

የበጀት፣ የሰው ኀይልና ሌሎች የግብዓት አቅርቦት ችግሮችም በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ነው የገለጹት።

የፍርድ ቤቶችን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የተገልጋይ ዕርካታ የዳሰሳ ጥናት ተጠናቆ በየደረጃው ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች መሰራጨቱንም ነው የተናገሩት።

ወደ ፍርድ ቤት ከሚመጡ ጉዳዮች መካከል ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የመሬት ጉዳዮች መኾናቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት ከመሬት ቢሮና ከክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት መሥራት ተችሏል ነው ያሉት።

ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ከቀረቡ ከ29 ሺህ 900 በላይ የሰበር፣ የወንጀልና የፍታ ብሔር ጉዳዮች ውስጥ 22ሺህ 500 ለሚደርሱ መዝገቦች ውሳኔ ተሰጥቷል ነው ያሉት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቱ አብየ ካሳሁን።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ እና የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሪፖርታቸውን ያቀረቡ ሲኾን ሌሎች ተቋማትም ለፍትሕና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የበጀት ዓመቱን የማጠቃለያ ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሏል።

ዘጋቢ:-ተስፋሁን ታምር

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በበጀት ዓመቱ ማዕድንን በሀገር ውስጥ በማምረት ከ144 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭን ማስቀረት ተችሏል” ማዕድን ሃብት ቢሮ
Next articleበ2016 ዓ.ም የአማራ አንደኛ ሊግ የሚሳተፉ ክለቦች ታውቀዋል።