
ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ማዕድን ሃብት ልማት ቢሮ የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለንግድ ፣ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል።
የቢሮው ኀላፊ ኃይሌ አበበ ባቀረቡት ሪፖርት በበጀት ዓመቱ የማዕድን ዘርፉን አስመልክቶ ለሚመለከታቸው አካላት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።
በክልሉ ያሉ የማዕድን ሃብቶች ላይ ጥናት ስለመደረጉም ነው በሪፖርቱ የገለጹት። በተደረገው ጥናትም በርካታ የማዕድን ሃብቶች ስለመገኘታቸው የገለጹት ቢሮ ኀላፊው ወርቅ፣ የደንጋይ ከሰል፣ ላይምስቶን ማዕድናት እና የመሳሰሉ ውድ የከበሩ ድንጋዮች በተለያዩ ቦታዎች ተገኝተዋል ብለዋል።
በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ወርቅን በማምረት ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ መቻሉን ነው በሪፖርቱ የተገለጸው።
ከውጭ የሚገቡ ማዕድናትን በሀገር ውስጥ አምርቶ በመተካት 144 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪን ማስቀረት መቻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
ጅብሰም፣ ፑሚስ፣ ላይምስቶን፣ ሊካሳንድ እና ሌሎችንም ማዕድናት በሀገር ውስጥ በማምረት ነው ከውጭ የሚገባን ማዕድን መተካት የተቻለው ተብሏል።
ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!