“ሌብነትና ብልሹ አሠራር የከተሞቻችን ዕድገት ፈተና ኾኗል” ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ

59

ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ የ11ወራት የዕቅድ አፈጻጸሙን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል።

ቢሮ ኀላፊው ቢያዝን እንኳኾነ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረቡት ሪፖርት በአገልግሎት አሰጣጥ ሥራው ሌብነትና ብልሹ አሠራር የከተሞቻችን የዕድገት ፈተና ኾኗል ብለዋል።

በአገልግሎቱ ዘርፍ ከባለሙያው እስከ አመራሩ የሌብነት ተግባር፣ አገልግሎት ፈላጊውም መደለያ የመስጠት ጉዳይ ያልተሻገርነው ችግር ኾኗል ነው ያሉት በሪፖርታቸው።

የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖር፣ ኅብረተሰቡ ጉዳዩን ለማስፈጸም ከመታገል በመደለያ ጉዳዩን ማስፈጸምን መምረጥ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከአመራር እስከ ባለሙያና አመራር ሰርቶ ሳይኾን ባልተገባ መንገድ የመበልጸግ አመለካከት እያደገ መምጣቱ የችግሩ ምንጭ ነው ተብሏል።

ሌብነትን እና ብልሹ አሠራርን ለመታገል የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የሚጠይቅ ይኾናል ነው ያሉት ኀላፊው።

ቢሮው 570 የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አቅዶ 433 ችግሮችን መፍታት ችሏል ብለዋል። 30 ሺህ 273 ሰዎች ያቀረቡት የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ምላሽ ተሰጥቶታል ነው ያሉት።

በሂደት ላይ ያሉትን ሳይጨምር በ16 አመራሮችና በ8 ባለሙያዎች ላይ ሕጋዊና አሥተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል ተብሏል በሪፖርቱ።

ሕገወጥ ግንባታ፣ የመሬት ወረራ በከተሞች ዙሪያ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሏል።

በበጀት ዓመቱ በ311 ከተሞች 88 ሺህ 241 ሕገወጥ ይዞታዎች ተደራጅተው የተያዙ ናቸው ተብሏል። ከዚህም 25 ሺህ 892 እንዲፈርሱ ተደርጓል ብለዋል ቢሮ ኀላፊው።

የአሠራር ሥርዓቱን ለማዘመን እየተሠራ መኾኑን በሪፖርታቸው ያቀረቡት ቢሮ ኀላፊው በከተሞች 3ሺህ 523 የመንግሥት ቤቶችን ወደ ሲስተም ማስገባት ተችሏል ብለዋል።

የመሬት መረጃንና አገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል ለማድረግ የሶፍት ዌር ማንዋል ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት ላይ ነው ተብሏል።

የከተሞችን የፋይናንስ አጠቃቀም በተመለከተም 155 ከተሞችን የፋይናስ አጠቃቀም ኦዲት ለማድረግ ታቅዶ በ11 ወራት149 ከተሞችን ኦዲት ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በተደረገው ኦዲትም 3 ሚሊዮን 575 ሺህ 518 ብር የተገኘን የኦዲት ጉድለት ተመላሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጣና ሞገዶቹ የዘንድሮውን የኢትዮጵያን ፕሪምየር
Next article“በበጀት ዓመቱ ማዕድንን በሀገር ውስጥ በማምረት ከ144 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭን ማስቀረት ተችሏል” ማዕድን ሃብት ቢሮ