
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 5/2012ዓ.ም (አብመድ) ተመራማሪዋ ከወዳደቁ የፕላስቲክ እና የመስታዎት ቆሻሻዎች የቤት ክዳን ጣሪያዎችንና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶችን እያመረቱ ነው፡፡
በኬንያ የፕላስቲክ ቆሻሻ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡
የኬንያ የአካባቢ ጥበቃ ተመራማሪዋ ሆፕ ማዋንኬ ‹ጊልጋይል› በተባለችው ከተማ ሲዘዋወሩ የፕላስቲክ፣ ጠርሙስ እና ጄሪካኖች በአካባቢው ነዋሪዎች፣ ሆቴሎች፤ ሱቆች፣ ትምህርት ቤቶች ተጥለው ክምር መሥራታቸውን ታዝበዋል፡፡ እናም ይህንን የቆሻሻ ክምር ወደ ሚጠቅም ነገር ለመቀየር እንዳነሳሳቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹ፕላስቲኮችን ሁሉ በዘፈቀደ ሜዳ ላይ ነው የምንከምረው፣ ይህ ጥሩ አይደለም፡፡ አሁን ግን የተሻለ መፍትሔ አግኝተንለታል›› ብለዋል ሆፕ ማዋንኬ፡፡
ተመራማሪዋ ‹‹በእነዚህ የተጣሉ ፕላስቲኮች የሆነ ነገር መሥራት ብዙ አስበን ከተመራመርን እና ሙከራ ካደረግን በኋላ በገበያ ተፈላጊ የሆነ ምርት በማምረት የፕላስቲክ ብክለት እንዲቀንስ ማድረግ ችለናል›› ብለዋል፡፡
ምዋንኬ ከንግድ ሥራ ባልደረባቸው እና ተጓዳኝ የአካባቢ ሳይንቲስት ኬቪን ሚሪቲቲ ጋር እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 “ኢኮ ብሎክ እና ታይልስ” የተባለ ኩባንያ አቋቋሙ፡፡ ኩባንያው ከኬሚካል እና ከመስታዎት ቆሻሻዎች የቤት ክዳንና ሌሎች የግንባታ ቁሳቁሶችን የሚያመርት የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
ከወዳደቁ ፕላስቲክ እና ብርጭቆ ቆሻሻዎች የተሠሩት የግንባታ ቁሳቁሶች ለረጅም ጊዜ የሚቆዩ፣ ቀላል፣ ለትራንስፖርት አመቺ ከኮንክሪት የተሻለ ለመዘርጋት የሚቀል መሆኑን የፈጠራ ባለቤቷ አስረድተዋል፡፡ ለዝናብ ውኃ ማጠራቀሚያነትም ምቹ ናቸው ተብሏል፡፡
የኬንያ ብሔራዊ የግንባታ ባለስልጣን በበኩሉ ‹‹በኬንያ እያደገ ካለው የሕዝብ ቁጥርና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመጣውን አቅምን ያገናዘበ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ማሟላት እና በ2050 (እ.አ.አ) የሕንጻዎችን የካርቦን ልቀት ዜሮ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት የገበያ አቅም ይሆናቸዋል ብሏል፡፡
እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየደቂቃው መጠጥ የያዙ አንድ ሚሊዮን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ግዥ ይፈጸማል፡፡
ከፕላስቲክ ማሸጊያዎች አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የቆሻሻ ማሰባሰብ ሥርዓቶችን በማምለጥ በየዓመቱ ቢያንስ ስምንት ሚሊዮን ቶን ፕላስቲክ ወደ ውቅያኖስ በመግባት ይበክላል። በተጨማሪም ፕላስቲክ የውኃ አቅርቦትና የምግብ ሰንሰለት ውስጥ በመግባት በረጅም ጊዜ ሰዎችን ይጎዳል፡፡
ምንጭ፡- የአልጀዚራ
በብሩክ ተሾመ