አምስተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚኩራ ክፍለ ከተማ አሥተዳደር ተካሂዷል።

76

አዲስ አበባ: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ችግኝ መትከል እንደ ሀገር አብሮነትን እና ወንድማማችነትን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ሲሉ የችግኝ ተከላ ተሳታፊዎች ተናግረዋል ።
የሀገሪቱን የደን ሃብት መልሶ ለመተካት እና የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ታላሚ ያደረገ ሥርዓት ለመገንባት በሚል ላለፉት አራት ዓመታት የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተካሂዷል።
በዚህ ዓመትም ይህ ፕሮግራም ተጠናክሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አሥኪያጅ ጽሕፈት ቤትና ተጠሪ ተቋማት በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ከ10 ሺህ በላይ ችግኞችን በዛሬው እለት ተክለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አሥኪያጅ ጥራቱ በየነና የ10ሩም ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ኀላፊዎችና ሠራተኞች፣ የ11ዱም የክፍለ ከተማ ሥራ አሥኪያጅ ጽሕፈት ቤት አመራሮች ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመኾን የችግኝ ተከላ አከናውነዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የፅዳት አሥተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዳሬክተር ሳዲቅ ሸኩር ችግኝ ተከላ ከአየር ንብረት ማስተካከል ባሻገር ዘርፈ ብዙ ጠሜታ አለው ብለዋል።
የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ ከከተማ ግብርና ጋር በመተባበር ፍሬ አፍርተው ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ አትክልቶች የተካተቱበት መኾኑን ተሳታፊዎች ለአሚኮ ሀሳባቸውን አጋርተዋል ።
የዛሬው ችግኝ ተከላ በመላው የሀገሪቱ ክፍል እየተተከለ ያለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አካል ነው ያሉት ተሳታፊዎቹ ችግኝ ተከላ የሕዝብን አብሮነት ለማጠናከር ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
ችግኝ መትከል ብቻውን ግብ አይደለም ያሉት ተሳታፊዎቹ የሀገር ሀብት የፈሰሰበትን ችግኝ ተከታትሎ እንዲጸድቅና ለሀገር ጥቅም እንዲውል መሠራት ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ አየለ መስፍን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጦርነቱ የተጎዳውን የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል መልሶ ለመገንባት የሚያገለግል የእርዳታ ማሰባሰቢያ ድረ ገጽ ማበልጸጉን አንበሳ ባንክ አስታወቀ።
Next article“በአማራ ክልል በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ5 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች ይሳተፋሉ” የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ