
አዲስ አበባ: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “አንበሳ ፈንድ” የተባለው የእርዳታ መተግበሪያ ፕላት ፎርም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ለተጎዱ የአማራ፣ የትግራይና የአፋር ዜጎችን ለማገዝ የተመሠረተ ነው ሲሉ የአንበሳ ባንክ ፕሬዚዳንት ዳንኤል ተከስተ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
አንበሳ ባንክ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን መወጣቱን አንዱ ማሳያ ይህ የእርዳታ ማሠባሠቢያ ፕላት ፎርም ማዘጋጀቱ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል ዲያስፖራው ይህን በጎ እድል በመጠቀም ሀገራቸውን ሊጠቅም ይገባል ብለዋል።
ባንኩ ከትረስትድ ቴክ ትሬዲንግ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ጋር በመተባበር አንበሳ ፈንድ የተባለ ዲጂታል የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ አበልጽጎ ወደ ትግበራ በመግባት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ዛሬ በይፋ የተመረቀው ይህ ድረገጽ በውጭ ሀገር የሚኖር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሞባይሉን ወይም ላፕቶፑን በመጠቀም ባመቸው ቦታና ሰዓት የፈለገውን ያህል የእርዳታ ገንዘብ ለመለገስ የሚያስችል ሲኾን በሀገራችን በተለያዩ ማኅበራዊ የአገልግሎት ዘርፍ የተሠማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ድርጅቶች ለሚነድፏቸው ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ የገንዘብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።
ይህ ፕላትፎርም በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሠራበት ከሚገኘው “ጎፈንድ ሚ ፕላት ፎርም” ጋር በዓይነቱ ተመሳሳይ በመኾኑ ማኅበራዊ ኀላፊነትን ለመወጣት ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ የገንዘብ እርዳታ ለማሰባሰብ ያስችላቸዋል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
የትረስትድ ቴክ ትሬዲንግ ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ሀብታሙ ታደሰ ይህን ሲስተም ማስተር ካርድ የሚጠቀም ደኅንነቱ የተረጋገጠ ነው ብለዋል። “WWW.ANBESAFUND.COM በቀላሉ መጠቀም የሚቻል በፍትሀዊነት ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ድረ ገጽ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ ለዚህ ተግባሩ አንበሳ ባንክን አመሥግነዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል ኪሮስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!