መንግሥት በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ቢያተኩር ችግሮች ሊቀንሱ እንደሚችሉ ወጣቶች ተናገሩ፡፡

147

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 05/2012ዓ.ም (አብመድ) በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአማራ ተወላጆች፣ የአማራ ወጣች ማኅበሩ አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ በውይይቱም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአማራ ወጣቶች ማኅበር ከፖለቲካ ገለልተኛ በመሆን የሚሠራ ማኅበር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ወደፊት ለጋራ ለውጥ እና ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባው ተወያዮች አሳስበዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአማራ ወጣቶች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ትልቅሰው ጥሩነህ እንደተናገረው ወጣቶች ከስብሰባና ውይይት ባለፈ የተወያዩትን መተግበር አለባቸው፡፡ ወጣቶች እንደ አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) ያሉትን የልማት ድርቶች በመደገፍ ለልማቱ የራሳቸውን አስተዋጾ ማበርከት እንደለባቸውም አሳስቧል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአማራ ወጣቶች ማኅበር ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንዳለው አብዩ ደግሞ ‹‹ወጣቱ ያልተገቡ ያለፉ ታሪኮች ላይ ትኩረት ከማድረግ ለወደፊት የራሱን ታሪክ መሥራት አለበት›› ብሏል፡፡ ወጣቱ ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ ሊወጣ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶችም ‹‹ወጣቱ ወደ ችግር እንዲገባ እያገፋፋ ያለው ጉዳይ ሥራ አጥነት ነው፤ መንግሥት የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የወጣቱን ተጠቃሚነት ማርጋገጥ አለበት›› ብለዋል፡፡ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ከተሰጠና ወጣቱ በሥራ እራሱን ከጠመደ የሚያጋጥሙ ችግሮች ሊቀንሱ እንደሚችሉ ነው ተወያዮቹ ያመላከቱት፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የአማራ ወጣቶች ማኅበር ‹‹በተደራጀ አንድነት አማራን ከገጠመው ችግር እንታደግ›› በሚል መሪ ሐሳብ ነው ዛሬ ውይይት ያደረጉት፡፡

ዘጋቢ ራሔል ደምሰው-ከአዲስ አባባ

Previous articleስለ ባለማተቧ ሕጻን ሳይንሳዊ ትርጓሜም ሆነ ማረጋገጫ ለመስጠት መቼገራቸውን የጤና ባለሙያው ተናገሩ።
Next article“በኩር” የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት የበኩር ልጅ፡፡