
አዲስ አበባ: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ11 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ከተቋቋመው ኖርዝ ኢስት ትሬዲንግ አክሲዮን በመግዛት ኢትዮጵያውያን ሀገርን እና እራሳቸውን አንዲጠቅሙ ትሬዲንግ አክሲዮኑ ጥሪ አቅርቧል።
ኖርዝ ኢትስ ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር በወሎ መካነ ሰላም እና አካባቢው ላይ መሰረት አድረጎ ለመሥራት የተቋቋመ ትሬዲንግ አክሲዮን ሲኾን የሚገኝን እምቅ አቅም አውጥቶ ለመሥራት ዓላማ ያለው አክሲዮን ማኅበር መኾኑ ተገልጿል
የኖርዝ ኢስት ትሬዲንግ አክሲዮን የአደራጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር አበራ ደሳለኝ አዋጭነታቸው የተለየ የዘይት፣ የሲሚንቶና ሌሎች ፋብሪካዎች ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ የተቋቋመ ነውም ብለዋል።
ዋና መነሻው “በአንድነት ወደ ከፍታ” የሚል ዓላማ ይዞ በመኾኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
የአደራጆች ሥራ አሥኪያጅ አምኃ ተገኝ ኖርዝ ኢስት አክሲዮን በሀገራችን ያልተሠራባቸው ዘርፎችን በመለየት ለመሥራት የተቋቋመ ነው ብለዋል። ይህንን ለመሥራትም ቅድመ ጥናት መሠራቱን አንስተዋል።
አክሲዮን ማኅበሩ በዋና ዋና የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚሠራ ሲኾን ቅድሚያ የተሰጠው የሲሚንቶ ምረት ስለመኾኑም ተገልጿል። በኢትዮጵያ በርካታ የሲሚንቶ ጥሬ ዕቃ እያለ ማምረት አለመቻሉን አንስተዋል። በመኾኑም አቅም ያላቸውን አካላት በማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን አንስተዋል።
የኖርዝ ኢስት ትሬዲንግ አክሲዮን የአደራጆች ፀሐፊ አሰግድ ኃብተሚካኤል አክሲዮኑ መሸጥ መጀመሩን ተናግረዋል። ማኅበሩ 11 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ይዞ ሥራዎችን ለመሥራት መቋቋሙንም ገልጸዋል።
ሰኔ 24/2015 ዓ.ም ጀምሮ አክሲዮኑ መሸጥ መጀመሩን የገለጸው ኖርዝ ኢስት ትሬዲንግ እሰከአሁን መሸጥ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ 110 ሚሊዮን ብር መሸጡን ገልጿል።
በዚህም ያለውን አቅም አሰባስቦ የኢትዮጵያን አቅም ለመጠቀም እና የሥራ እድል ለመፍጠር ያለመ በመኾኑ አክሲዮን በመግዛት ይህንን እድል አንዲጠቀሙ ሀገራቸውንም አንዲጠቅሙ ማኅበሩ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም በእጣን፣ በኦፓል ማእድን እና በሌሎች የግብርና ዘርፎች ለመሰማራት ዓላማ አለው ነው የተባለው።
የኖርዝ ኢስት ትሬዲንግ አክሲዮን የአደራጆች አባል እና የቴክኒክ ክፍል ኀላፊ ኢንጅነር የኋላው ሲሳይ ሽያጭ መጀመሩን ገልጸው ከዝቅተኛው 10 ሺህ ብር አስከ ከፍተኛው 50 ሚሊዮን ብር በሁሉም ባንኮች መግዛት አንደሚቻል ተናግረዋል።
እሰከአሁን አስፈላጊውን የመንግሥት ፈቃድ ወስዶ የቦታ ርክክብ ማድረጉንም አስገንዝበዋል። በቴክኒክ ዘርፉ በኩልም ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር እየተደራደረ መኾኑን አንሰተዋል።
ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!