
ደባርቅ: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ወይዘሮ ፈንታ ተስፉ በጃንአሞራ ወረዳ መካነ ብርሃን ከተማ የደርስጌ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናትም ናቸው። ወይዘሮ ፈንታ ጠላ ጠምቆ በመሸጥ ሕይወታቸውን ይመራሉ።
በአካባቢያቸው የተከፈተው የሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውኃ (ቦኖ) በሌሊት ወጥቶ ምንጭ ላይ ጊዜያቸውን ከማጥፋት አውጥቷቸዋል። ዛሬ ተራቸው ሲደርስ በቀን ሁለት ጀሪካን ውኃ ይቀዳሉ። ተራቸው ካልኾነ እንጀራዬ ያሉት ሥራ እንዳይቋረጥ ወንዝ ወርደው መቅዳታቸው አልቀረም። በውኃ እጦት ምክንያት የጠመቁት ጠላ ሳይሸጥ በመቅረቱ ወረታቸው መክሰሩ የቅርብ ጊዜ ትዝታቸው ነው። የተዘረጋው ውኃ ድፍን የከተማው ማኅበረሰብ የሚጋራው በመኾኑ ሁሉንም ለማዳረስ አቅም የለውም። የሚከፈትበት ሰዓት በቀን ለሁለት ሰዓት የተገደበ ነው። በርካቶች ከ12 ሰዓት እስከ 2 ሰዓት ወረፋ ሲጠብቁ አርፍደው ባዶ ጀሪካን ይዘው ይመለሳሉ። የውኃው አቅም ቢጨምር እና እንደልባቸው ቢቀዱ ጊዜአቸውን ጉልበታቸውን እንደሚቆጥብላቸው ተናግረዋል። ገቢያቸውን ለማሳደግ ሥራቸውን አስፋፍተው ለመሥራት እቅድ ቢኖራቸውም የውኃ ችግሩ አለላውስ ብሏቸዋል።
ሌላዋ ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን(አሚኮ) ሃሳባቸውን የሠጡት ወይዘሮ ባንችዬ ስመኝ በጃንአሞራ ወረዳ የደረስጌ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ባለትዳር እና የሦስት ልጆች እናት ናቸው። አራስ ልጃቸውን አዝለው ወረፋ ይጠባበቃሉ። ከደረሳቸው ይቀዳሉ ካልደረሳቸው ሳይቀዱ ይመለሳሉ። ወይዘሮ ባንችዬ እና መሰሎቻቸው የሚፈልጉትን ያህል ውኃ አግኝተው አያውቁም። በበጋ ውኃ የሚያገኙ በአራት ቀን አንድ ቀን ነው። አሁን ክረምት በመኾኑ ዕቃ ለማጠቢያ የሚውል ይቀዳሉ። “በቀን ሁለት ጀሪካን ውኃ ተቀድቶ ለየትኛው ሥራ ይበቃል? የልጆች ልብስ ይታጠባል፣ ምግብ ይበሰላል፣ ቤት ይጸዳል፣ ለየትኛውም ሥራ አይበቃም” ይላሉ ወይዘሮ ባንቺዬ። አራስ ሥለኾንኩ እንደልቤ ወንዝ አልወርድም፣ መንገዱ ውጣ ውረድ ያለበት በመኾኑ ጉልበቴም ይብረከረካል ብለዋል። ሠፈራቸው ድረስ የመጣው የቦኖ ውኃ አቅሙ ጨምሮ እንደልባቸው እንዲቀዱ የሚመለከተው አካል የድርሻውን እንዲወጣም ጠይቀዋል።
የመካነ ብርሃን ከተማ ውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሥራ አሥኪያጅ ወርቁ ጸጋው ከከተማዋ ሕዝብ ጋር የሚቀራረብ የውኃ አቅርቦት አለመኖሩን ገልጸዋል። 23 ኪሎ ሜትር አቋርጦ የሚመጣውን ውኃ በፍትሃዊነት ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ውኃው በተለያዬ ጊዜ አደጋ ይገጥመዋል። ችግሩን ለመፍታት ሞክረናል ይላሉ። ካሁን ቀደም በ45 ቀን ይደርስ የነበረውን የውኃ ወረፋ የሰሜን ጎንደር ዞን ውኃ እና ኢነርጅ ቢሮ ባደረገው ድጋፍ ወደ 15 ቀን ዝቅ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል። ታንከሮቹን ለመሙላት 16 ሰዓት ይፈጅ የነበረው ጄነሬተር ወደ 7 ሰዓት ዝቅ ብሏል ይላሉ። ይሕ በቂ አይደለም የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውኃ ፍላጎት ለማሟላት ሌላ የውኃ ጉድጓድ ያስፈልጋል ብለዋል። ወረዳው ዘላቂ መፍትሔ ባያመጣም ያለውን ውኃ በፍትሃዊነት በማዳረስ ተጠቃሚ እያደረግን ነው። የሚመለከተው አካል ተጨማሪ የውኃ ተቋም በመገንባት ችግራችንን ቢፈታልን ሲሉ ጠይቀዋል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ውኃ እና ኢነርጅ መምሪያ ኀላፊ አምሳሉ አየልኝ የጃን አሞራ ወረዳ መካነ ብርሃን ከተማ የውኃ ፍላጎትን ለማሟላት በ15 ሚሊዮን ብር ጉድጓድ ተቆፍሮ ከነባሩ መሥመር ጋር በመጨመሩ የውኃ ወረፋውን ከ45 ቀን ወደ 15 ቀን ዝቅ ማድረግ ተችሏል ይላሉ። 5 ነጥብ 5 ሊትር በሰዓት የሚያመርት ምንጭ መገንባቱንም ተናግረዋል።
ዞኑ የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውኃ ፍላጐት ለማሟላት ጥናቱን አጠናቆ ዲዛይኑን ለክልሉ አቅርቧል፣ ክልሉም ጥናቱን ተቀብሎ በጀት የማፈላለግ ሥራ እየሠራ መኾኑን አስረድተዋል። ይሕ የንጹህ መጠጥ ውኃ ተቋም ተገንብቶ ሲጠናቀቅ የከተማዋን የውኃ ችግር መቶ በመቶ ይቀርፋልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!