“በበጀት ዓመቱ በአማራ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለኾኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል” ሥራና ሥልጠና ቢሮ

51

ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የንግድ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚከታተላቸውን ተቋማት የ2015 በጀት ዓመት የ11 ወር ዕቅድ አፈጻጸም እየገመገመ ነው።

የአማራ ክልል ሥራና ሥልጠና ቢሮ የ11 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለቋሚ ኮሚቴው አቅርቧል።

ቢሮ ኀላፊው አረጋ ከበደ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር የሥራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት ተሠርቷል።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ ለ1 ሚሊዮን 203 ሺህ180 ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር አቅዶ ለ 1ሚሊዮን 9 ሺህ 707 ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።

የእቅዱን ከ90 በመቶ በላይ መፈጸም ተችሏል ነው ያሉት ቢሮ ኀላፊው።

ከዚህም ከ743 ሺህ በላይ ዜጎች በቋሚነት የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ሲኾን ከ350 በላይ የሚኾኑት ደግሞ በጊዚያዊነት የሥራ እድል የተፈጠረላቸው ናቸው ተብሏል በሪፖርቱ።

በግብርና፣ በኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች በዋናነት በርከት ያለ ቁጥር የሥራ እድል መፍጠር እንደተቻለም ተመላክቷል።

ከውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘም በክልሉ 81 ሺህ 802 ዜጎችን መመዝገብ እንደተቻለ ነው የተናገሩት።

ከተመዘገቡትም ከ30 ሺህ በላይ ሥልጠናውን ወስደዋል ተብሏል።

ከዚህም 5 ሺህ 342 ዜጎች ሰልጥነው የሚሰጠውን የመመዘኛ ፈተናውን አልፈው ወደ ውጭ ሀገር ሂደዋል ነው የተባለው።

በቀረበው ሪፖርት መሰረት የቢሮው አጠቃላይ የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በቋሚ ኮሚቴ አባላት ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክረምቱ የበጎ ፈቃድ ሥራ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) አሳሰቡ።
Next article“የባሕል ፌስቲቫሉ የተሳሳቱ ትርክቶችን አርሞ የሕዝባችንን እውነቶች ለማሳየት ኹነኛ መንገድ ነው” ጣሂር ሙሐመድ