
ባሕር ዳር: ሐምሌ 01/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ክልላዊ የክረምት የወጣቶች በጎፈቃድ አገልግሎት የመክፈቻ መርኅ ግብር “በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ ” በሚል ሃሳብ በባሕር ዳር ከተማ ተጀምሯል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ.ር) የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ ግብርን አስጀምረዋል።
ርዕሰ መሥተዳደሩ እንዳሉት በክልሉ በክረምቱ ወራት የሚደረገው የበጎ አድራጎት ሥራ የቆየውን የሀገሪቱን የመረዳዳት ባሕል የሚያጠናክር ነው። በክረምት የሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ለአየር ንብረት ለውጥ ሚናው የጎላ በመኾኑ የሚተከሉ ችግኞችን ከመትከል ባለፈ መንከባከብ ይገባል ብለዋል።
የሀገራችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ፣ በደም ልገሳ፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝና የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በክረምቱም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች ማኅበረሰቡን በማነቃነቅ ይተከላልም ተብሏል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!