
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ውስጥ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ታላሚ ያደረገ ነው የተባለለት ዓውደ ጥናት አካሂዷል፡፡
በዓውደ ጥናቱ “የግል ትምህርት ቤቶች አበርክቶ፣ ተግዳሮትና መፍቻ መንገዶች” በሚል ርእሰ ጉዳይ ጥናታዊ ጹሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ባለሃብቶች በግል ትምህርት ላይ መዋእለ ንዋያቸውን የሚያፈሱት ትርፍን ብቻ ታላሚ አድርገው ሳይኾን ለትውልድ ግንባታው ሚናቸውን ለመወጣት ስለመኾኑ በመድረኩ ተወስቷል፡፡
ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶክተር የሻንበል አጉማስ የትምህርት ጥራት ትብብራዊ አሠራርን የሚጠይቅ፣ ጥራትን ለማስጠበቅም ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር የሚፈልግ ነው ብለዋል፡፡
በዘርፉ ሥልጣኔንና ዝማኔን ከመሻት እስከ ማሳለጥ ባለው ሂደት የትምህርት ዋጋን በሚመጥን ደረጃ መሥራት እንደሚያስፈልግም በአጽንኦት አንስተዋል፡፡
የግል ትምህርት ቤቶች በሚናቸው ልክ ከሠሩ ሀገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው የሚሉት ዶክተር የሻንበል የትምህርት ተደራሽነትን በማስፋት፣ ጥራትንና አግባብነትን በማረጋገጥ፤ ብቁ ዜጎችን በማፍራት፤ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እና የሥራ እድል በመፍጠር ረገድ አበርክቷቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር የሻንበል ባቀረቡት ጽሑፍ የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት ጋር በተዋረድ የሚገናኙበት የአሠራር ሰንሰለት ክፍተት፤ ለትምህርት ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ፈጣን ምላሽ አለማግኘት፤ የፖሊሲ፣መመሪያና ሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት የግል ትምህርት ቤቶች አለመሳተፍ እና እንደ ገንዘብ ሰብሳቢ ተቋም ተደርግው መወሰዳቸውን በችግር አንስተዋል፡፡
መንግሥት የግል ትምህርት ዘርፉ የተቋቋመበትን ዓላማ እንዲያሳካ ድጋፍ፣ ክትትልና ቀጥጥርን በዕውቀት መምራት እንደሚገባውም አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የሰላም አርጊው ቅድስት ማርያም አካዳሚ የወላጅ መምህራን ኀብረት ሰብሳቢ አቶ ዓለም ሁነኛው መንግሥት በተግባር የግል ትምህርት ቤቶች ምን ቁመና ላይ እንዳሉ መከታተል አለበት ባይናቸው፡፡
ወላጅ ተቸግሮም ቢኾን ልጁ የተሻለ ዕውቀት እንዲያገኝ ነው የግል ትምህርት ቤት የሚያስተምር የሚሉት አቶ ዓለም ከሕግና መመሪያ ያፈነገጠን ፤ ለትምህርት ጥራት ትኩረት የማይሠጥን የግል ትምህርት ቤት መንግሥት ሥርዓት ማስያዝ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ የወላጅ መምህራን ኀብረት ካላግባብ፣ ከተግባቦት ውጭ የኾነ የትምህር ክፍያ ጭማሪ እንዲኖር አንፈቅድም ነው ያሉት ሰብሳቢው። የተሻለ ትምህርት ቤት ለማንበር መምህራን፣ ርእሳነ መምህራንና የትምህርት አሥተዳደር፣ የወላጅ መምህራን ኀብረት በተቀናጀ መልኩ ከሠሩ የሚያኮራ ተግባር መፍጠር እንደሚቻል ነው ያነሱት፡፡
አቶ አብዮት ብርሃን በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር ምክትል ሰብሳቢ ናቸው፡፡ ለአሚኮ በሰጡት ማብራሪያ በግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ እና ሚናቸውን እንዲወጡ የመንግሥት ድጋፍና ክትትል ይገባል ነው የሚሉት፡፡
ትምህርት ቤቶች ከሰው ኀይል እስከ ቁሳቁስና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል የሚሉት አቶ አብዮት ፤ ከደረጃ በታች ያሉ ትምህርት ቤቶችን መለየት፣ መደገፍና ከችግሮቻቸው እንዲላቀቁ ማድግ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የትምህርት ዘርፉ በግብዓት፣ በሂደትና በውጤት የታጀበ መኾን አለበት የሚሉት ምክትል ሰብሳቢው ለዚህ ደግሞ መንግሥትም ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።
ማኅበሩ 41 አባል የግል ትምህርት ቤቶች እንዳሉት የተናገሩት አቶ አብዮት የተዘጋጀው ዓውደ ጥናት በግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ አስቻይ ግብዓንትን ለማግኘት ታሳቢ ተደርጓል ነው የሚሉት፡፡
ማኅበሩ “የግል ትምህርት ቤቶች ሀገር ወዳድ፣ ሀገር አሻጋሪ ዜጋ ለመፍጠር ሚናቸውን እንዲወጡ እየሠራን ነው “ብለዋል፡፡ ከደረጃ በታች የኾኑ አባል ትምህርት ቤቶች እንዳሉ የተናገሩት ምክትል ሰብሳቢው እንዲያሻሽሉም ማኅበሩ እገዛ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ከትርፍ ባሻገር የኾነ ሚናቸውን እንደሚወጡም ነው ያስረዱት።
በግል ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ፣ የተማሪዎች በዕውቀትና ሥነ-ምግባርን የተሻሉ እንዲኾኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እናደርጋለን ያሉት ደግሞ የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ኃይለማሪያም እሸቴ ናቸው፡፡
መንግሥት ከደረጃ በታች የኾኑ ትምህርት ቤቶች ማሻሻል ሥራው ላይ እንዲያተኩሩም እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
ከደረጃ በታች ኾኖ መቀጠል አይቻልም የሚሉት መምሪያ ኀላፊው መንግሥት ደረጃቸውን በማያሻሽሉ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት፡፡
በመመሪያው እና በሕጉ መሠረት የማይዳኝ የግል ትምህርት ቤት ካለ የሥራ ዘርፉን እንዲቀይር እንመክራለን እንጂ በዝምታ አናልፍም ነው ያሉት፡፡
በውይይትና በምክክር ያልኾነ ትርፍን ብቻ ታሳቢ ያደረገን የትምህርት ክፍያ ላይ ያተኮሩ የግል ትምህርት ቤቶችን ተጠያቂ እንደሚያደርጉም ነው የተናገሩት፡፡
የግል ትምህርት ቤቶች ለመንግሥት የሚያነሱትን ጥያቄ መፍትሔ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሠራም ነው ያስረዱት፡፡
ዘጋቢ፡-ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!