
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ በሰጡት መግለጫ የአማራ ክልል ሕዝብ በእጅጉ ሰላም እንደሚሻ ገልጸዋል፡፡ የአማራ ክልል የመልማት እድል እና አቅም ያለው ክልል በመኾኑ ለልማት ምቹ አጋጣሚዎችን መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ የአማራ ሕዝብ እና መንግሥት የሰላምን ዋጋ በቅጡ የሚገነዘብ፣ ለሰላም ዋጋ የሚከፍል፣ ሰላምን ከሁሉም የሚያስቀድም መኾኑንም አንስተዋል፡፡
የአማራ ክልል በየጊዜው ሰላሙን የሚፈታተኑ ጉዳዮች የሚገጥሙት ክልል ነው፡፡ የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ግን የሚገጥሟቸውን ፈተናዎች እና ችግሮች እየተቋቋሙ ልማቱን እያከናወነ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ልማት እየተካሄደ ነው ማለት ችግር የለበትም ማለት አይደለም ያሉት ኃላፊው ውጫዊ እና ውስጣዊ ጫናዎች የሚበረቱበት፣ ችግሮችን ባልተገባ መንገድ የሚያራግቡ የሚበዙበት፣ በቀላል መፈታት የሚቻሉ ጉዳዮች ወደ አልተገባ መንገድ የሚሄዱበት ሂደት ይስታዋላል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ አብዛኛው አካባቢ ሰላሙን ጠብቆ ያለ ቢኾንም በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሮች አሉ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም አይገቡም፣ የደኅንነት ስሜት አይሰማቸውም፤ አንዳንድ አካባቢዎች የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፉ አደገኛ አካሄዶች መኖራቸውን ነው ያነሱት፡፡
ሰላም በጠፋ ቁጥር ተስፋ የተጣለባቸው ልማቶች እንዳይከወኑ፣ የአማራ ክልል ባለውሃብትና አቅም ልክ እንዳይለማ ያደርገዋል፡፡ የሰላም እጦትና ያልተገቡ አካሄዶች በሰፉ ቁጥር ከድኅነት ለመውጣት የሚተጋውን ሕዝብ በድኅነት እንዲኖር መፍረድ፣ ወጣቶች ሥራ እንዳይኖራቸው ማድረግ፣ የልማት እንቅስቃሴዎች እንዳይኖሩ መከልከል ነውም ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነቱን ለማሸነፍ ትግል በሚደረግበት በዚህ ወቅት ሰላምን ማወክ የበለጠ ለችግር መጋለጥ ነው ብለዋል፡፡ ይህ አካሄድ ክልሉን ቁልቁል የሚጎትት፣ አንገት የሚያስደፋ ስለሚኾን ለሰላም መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሰላም ለሁሉም እንደኾነች ሁሉ፤ ሁሉም ለሰላም መሥራት እንደሚገባውም ገልጸዋል፡፡
ባልተገቡ አካሄዶች የአማራ ክልል ሕዝብ አሁናዊ ጥያቄዎችም ኾኑ የሰነበቱ ጥያቄዎች መፍታት እንደማይቻል ያነሱት አቶ ግዛቸው ያልተገቡ አካሄዶች ሕዝብን እንደ ሕዝብ የሚያሳንሱ፣ ችግሮችን የበለጠ የሚያውሰብስቡ ናቸውም ብለዋል፡፡ ሰከን ብሎ ችግሮችን በውይይት መፍታት ተመራጩና አስፈላጊው መንገድ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ የክልሉ ሕዝብ የማንነት ፣ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ የዜጎች መብት፣ የተዛባውን ትርክት የማረም እና ሌሎች ጥያቄዎች እንዳሉበት ያነሱት ኃላፊው እነዚህን ጥያቄዎች ለመፍታት የውስጥ አንድነትን ማጠናከር ላይ ማተኮር ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡
ብስለት ያለውና ብልሃት የተመላበት የሃሳብ ትግል ማድረግ ሲቻል የአማራ ሕዝብ የዋሉ ያደሩና አሁናዊ ችግሮች እንደሚፈቱም አንስተዋል፡፡ አንድነት ከሌለ ልንደመጥ አንችልም፣ ጥያቄዎቻችን ሊመለሱ አይችሉም ነው ያሉት፡፡ መደማመጥ፣ መከባበር፣ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት፣ ከኃይል ይልቅ መነጋገርን ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በውይይት ተጽዖኖ ፈጣሪ ኾኖ ጥያቄዎችን ለመፍታት በጋራ መቆም ይገባል ነው ያሉት፡፡
መንግሥት የሰላም አማራጮችን ቅድሚያ በመስጠት ሕግ እንዲከበር ይሻል ያሉት ኃላፊው ሕግ እንዲከበር አማራጮችን እየተጠቀመ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የሕግና ሥርዓት መከበር ሕዝቡን እና መንግሥትን እንደሚጠቅምም ተናግረዋል፡፡ ሰላምና መረጋጋትን ሳናረጋግጥ ጥያቄዎቻችን ይፈታሉ፣ ያለው ስጋት ይቀረፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም ብለዋል፡፡ ለሰላም ሁሉም መተባበር አለበት፣ ለሰላም ሁሉም ዘብ መቆም አለበትም ብለዋል፡፡ ከሰላማዊ አማራጮች ውጭ ያሉ አካሄዶች ትክክለኛ እና አዋጭ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ከሰላማዊ አካሄድ ውጭ ያሉ አማራጮች ክልሉን እየጎዱት ነውም ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት በስሜት ሳይኾነ በስሌት፣ በኃይል ሳይኾን በሃሳብ ብልጫና በውይይት፣ በሕጋዊ አካሄድ መሄድ ነው መፍትሄው ብለዋል፡፡
ሕግና ሥርዓትን በማክበር በስክነት እና በአንድነት መሥራት ግድ ይላልም ነው ያሉት፡፡ ክልሉ ስኬቶችና ፈተናዎች የነበሩበትን ዓመት ማሳለፉን ያነሱት አቶ ግዛቸው አደጋዎችን እየቀነሱ ተቀራርቦ መሥራት አስፈላጊ ነውም ብለዋል፡፡
እንደ አቶ ግዛቸው ገለጻ የአማራ ክልል ችግሮች ውስጣዊውም ውጫዊም ናቸው፡፡ ውጫዊ ችግሮችን ለመፍታት ታዲያ ውስጣዊ ችግሮችን ማከም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን አርሞና አክሞ፣ በውስጣዊ ጉዳይ መግባባት ከተቻለ ውጫዊ ችግሮችን መቋቋም ይቻላል ነው የሚሉት፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን መፍታት በኢኮኖሚና በፖለቲካ ጠንካራ ያደርጋል፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ጠንካራ መኾን ሲቻል ተሰሚነት ይጨምራል፣ መደመጥና ጫና መፍጠሩ ከፍ ይላል ይላሉ፡፡
በክልሉ ውስጥ የተግባርና የአመለካከት አንድነት ፈጥሮ በመሄድ በኩል ጉድለቶች አሉ ነው ያሉት፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ውስጣዊ ችግሮችን የመፍታት ጽኑ እምነት እና አቋም አለው፣ ውስጣዊ ችግሮችን መፍታት የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት እድሎችን ይፈጥራሉ ነው ያሉት፡፡ በውስጣዊ ጉዳይ አንድ ሳትኾን፣ እርስ በእርስ ሳትተማመን እና እርስ በእርስ እየተገዳደልክ ውጫዊ ጠላቴን እመክታለሁ፣ ጥያቄዎችንም አስመልሳሉ ማለት የማይኾን ስሌት ነውም ይላሉ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ በአጀንዳዎቻችን ላይ እንተማመን፣ በችግሮቻችን መፍቻ መንግድ ላይ እንግባባ፣ የአንድነት፣ የመደማመጥ እና የመከባበር ችግሮቾን መፍታት ይገባል ብለዋል። የክልሉን አንኳር ጥያቄ ለማስመለስ ጠንካራ አንድነት መፍጠር ግድ ይላል ነው የሚሉት፡፡
መደበኛ ተቋማትን እያጠናከሩ ፣ ጥፋተኞን ለሕግ እያቀረቡ መጓዝ ለሕዝብና ለመንግሥት ጠቃሚው ጉዳይ ነው፡፡ የሰው ሕይዎት ከመጥፋቱ፣ ንብረት ከመውደሙ፣ ልማት ከመስተጓጓሉ አስቀድሞ ሁልጊዜም በውይይት ችግሮችን መፍታት ይገባልም ነው ያሉት፡፡ በስሜት መናጥና የውስጥ አንድነትን ማናጋት ለጠላትም ተገማች ያደርጋል ብለዋል አቶ ግዛቸው፡፡
የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት ለአፍታ እንኳን ባለመዘንጋት በትኩረት እየተሸራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎችን ትቶ ሕዝብን መምራት አይቻልም፣ ጥያቄዎቹ ለዘመናት ዋጋ የተከፈለባቸው፣ የሰው ሕይወት የተገበረባቸው፣ በቀላሉ ድርድር ውስጥ የሚገባባቸው አይደሉም፣ ጥያቄዎችን ለመፍታት በስፋት እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እስካልተመለሱ ድረስ የአማራ ክልል መንግሥት አርፎ አይተኛም፡፡ የአማራ ሕዝብ የተሰራበትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ወረቅት ላይ ብቻ ሳይኾን ከአዕምሮ ላይ ሁሉ የማስወገድ ሥራ በትኩረት መስራት ይገባዋል፣ ለዚያም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል፡፡
የኑሮ ውድነት እንዳይኖር ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት ኃላፊው ሰላም ሲከበር ምርት በነጻነት ከቦታ ቦታ ይተላለፋል፣ ሰላም ሲከበር ሕገ ወጥ የምርት እንቅስቃሴ ይቀራል፣ ኑሮውም ማረጋጋት ይቻላል ነው ያሉት፡፡ የኑሮ ውድነትን በዘላቂነት ለመፍታት ሰላምን መጠበቅና ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ይገባልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!