ሰኔ 30 እና ትዝታው!

36

ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሰኔ 30 በበርካቶች ዘንድ የማይረሳ ትውስታ እና ትዝታ ያላት ቀን ናት፡፡ አዲስ የሕይዎት ምዕራፍን በመጀመር እና ለሌላ የሕይዎት ምዕራፍ በመዘጋጀት የሰው ልጅ የሕይዎት እጥፋት የማዕዘን ቦታ ተደርጋ ትወሰዳለች፤ ሰኔ 30 ቀን፡፡

ለዓመታት የዘለቀ እልክ አስጨራሽ የሕይዎት ጉዞ የሚጠናቀቅባት እና ለሌላ የሕይዎት ምዕራፍ ጉዞ ዝግጅት እረፍት የሚወሰድባት የመጀመሪያ ቀን ናት ይባላል፡፡ ደመና ባዘለ ሰማይ ስር፣ ዝናብ በሚያካፋበት ቀን፣ በራሰ ምድር እና ቅዝቃዜ ባጠላበት ወቅት እጅግ የማይረሳ የህጻናት እና ወጣቶች ቡረቃ ከግራ ቀኝ ይሰማል፡፡ ተማሪዎች ለአንድ ዓመት የወጡ የወረዱበትን የትምህርት ጉዞ በይፋ አጠናቀው የሁለት ወራት እረፍ የሚጀምሩባት ቀን በመኾኗ ተወዳጅ እና ከትዝታ ማኀደር የማትጠፋ ቀን ያደርጋታል፡፡

በበርካታ አካባቢዎች የአንድ ክፍል ተማሪዎች በአንድ ኾነው አቅማቸው በፈቀደ ልክ በዝግጅት ይሰነባበታሉ፡፡ “በደህና ሁኑ በደህና ሁኑ፤ መለያያችን ደረሰ ቀኑ” እያሉ ያለፉትን 10 ወራት በዜማ እየሸኙ መጻዒዎቹን ሁለት የእረፍት ወራት ለመቀበል ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ በትምህርት ዝሎ የከረመ አዕምሮ ቀጣዩን የትምህርት ዘመን በአዲስ መንፈስ እና ዝግጅት ለመቀበል ከሰኔ 30 ጀምሮ እረፍት ያደርጋል፡፡ ሰኔ 30 በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ ያለፉ ሁሉ የማይዘነጓት ቀን ተደርጋ ትወሰዳለች፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያዊያን አቆጣጠር የሰባት ቀናት ልዩነት ቢኖረውም የጎርጎሮሳዊያኑ ሰኔ 30 ቀንም መደበኛ የትምህርት መዝጊያ ቀን ከመኾኑ ባሻገር “የአፍሪካ ሳይንሳዊ ሕዳሴ ቀን” እየተባለም በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡

የዘንድሮው የአፍሪካ ሳይንሳዊ ሕዳሴ ቀን (Africa Scientific Renaissance) ሲከበርም አጀንዳው ትምህርት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት መኾኑን በማስታወስ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአፍሪካ ሳይንሳዊ ሕዳሴ ቀን ሲከበርም በግጭት፣ በመፈናቀል፣ በአካል ጉዳት፣ በመሠረተ ልማት ውድመት፣ እንዲሁም በኑሮ ውድነት እና በሌሎች ምክንያቶች ከትምህርት ውጪ ኾነው ለበርካታ ወራት የቆዩ ሕፃናትን በ2016 ዓ.ም ወደ ትምህርት እንዲመለሱ የማድረጉ ሥራ ከፍተኛ እና የተቀናጀ ትኩረት እንዲሰጠው በማመላከት ነው፡፡

ትምህርት የማግኘት መብት ሰፊና በርካታ ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች የሚዳስስ እና መሠረታዊ ከኾኑ የሰብዓዊ መብቶች መካከል የሚመደብ መብት ነው። ትምህርት የማግኘት መብት ራሱን ችሎ መሠረታዊ የኾነ ሰብዓዊ መብት ከመኾኑ ባሻገር ሌሎች መሠረታዊ መብቶች እንዲሟሉ መሠረት የኾነ መብት ነው፡፡ መማር በራሱ ነጻነትን ማውጅ በመኾኑ፡፡ ትምህርት የማግኘት መብት አልተከበረም ማለት ሌሎች መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ተጥሰዋል እንደማለት ነው ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡

ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት፣ የማኀበራዊ እና የባሕል ቃል ኪዳን በአንቀጽ 13/1 ላይ አባል ሀገራት ሁሉም ሰው ትምህርት የማግኘት መብት እንዳለው ዕውቅና እንደሰጠ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ሀገራት የትምህርት ተቋማትን በየደረጃው እንዲያስፋፉ፣ ብቃት ያለው ነጻ የትምህርት ሥርዓት እንዲመሠርቱ እና የመምህራንን የኑሮ ኹኔታ ያለማቋረጥ እንዲያሻሽሉ ይጠይቃል።

የተባበሩት መንግሥታት ዘላቂ የልማት ግቦችም በግብ 4 ሥር ትምህርት ለዘላቂ ልማት ያለውን አስተዋጽዖ አስቀምጧል። ትምህርት የማግኘት መብት ሲባልም መገኘት፣ ተደራሽነት፣ አካባቢያዊ ተደራሽነት፣ ተቀባይነት እና ተስማሚነት እንደኾኑ ተደንግጓል፡፡

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ አንቀጽ 26/2 እና የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ እና የባሕል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 13 እንደተደነገገው ትምህርት የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ እድገት ማለትም አካላዊ፣ አእምሯዊ እና ሥነ-ልቦናዊ እድገት የማምጣት ዓላማ አለው። በሕዝብ እና በሃይማኖቶች መካከል መግባባትን፣ መቻቻልን እና ወንድማማችነትን በማምጣት ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ሌላው የትምህርት መብት ግብ ነው ተብሎ ተቀምጧል። ትምህርት የሰውን ስብእና እና ክቡርነት ለማሳደግ በሚያስችል አቅጣጫ መመራት፤ ለሰብዓዊ መብቶች እና መሠረታዊ ነጻነቶች የሚሰጠውን ክብር ማጠናከር ይኖርበታል ይላል፡፡

ሰኔ 30 ላይ ኾነን በጦርነት እና በኑሮ ውድነት መካከል መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት መገለጫ የኾነውን ትምህርት ያላገኙ ህጻናት እና ታዳጊዎች በቀጣይ ዓመት እንዲያገኙ በጋራ መሥራትን እና ትብብርን ይጠይቃል እንላለን፡፡ ከ80 በመቶ በላይ ከደረጃ በታች የኾኑትን የክልሉን የትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻል እና የትምህርት እድል ያላገኙትን ህጻናት የትምህርት እድል እንዲያገኙ ማድረግ የእረፍት ብቻ ሳይኾን የትጋትም ወቅት መኾኑን ያሳያል እንላለን፡፡

በታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ
Next article“ከሁሉ አስቀድሞ በአጀንዳዎቻችን ላይ እንተማመን፣ በችግሮቻችን መፍቻ መንገድ ላይ እንግባባ” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ