
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ከወትሮው በተለየ እጨመረ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡ በወቅታዊ የአማራ ክልል ጉዳይ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በኢንቨስትመነት ዘርፉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሰላም እንቅስቃሴ በሰፋ ቁጥር የልማት አማራጮች እንደሚሰፉም ተናግረዋል፡፡ በአማራ ክልል ከሌላው ጊዜ በተሻለ የኢንቨስትመንት ፍሰት መታየቱንም ገልጸዋል፡፡ 4 ሺህ 724 ባለሃብቶች በክልሉ የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተዋል ነው ያሉት፡፡ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ያወጡት ባለሃብቶች ከ483 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት ለ1 ሺህ 288 ባለሃብቶች ከ32 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ማስተላለፍ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
ሥራቸውን አጠናቅቀው ወደ ሥራ የገቡ ኢንቨስትመንቶች መኖራቸውንም ነው ቢሮ ኀላፊው የገለጹት፡፡ በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ከ80 ሺህ ቶን በላይ ምርት በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ138 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አስገኝተዋልም ብለዋል፡፡ የተገኘው ውጤት አስደሳች ነው ያሉት ኃላፊው ውጤቱን የበለጠ እያጠናከሩ መሄድ ይጠይቃልም ነው ያሉት፡፡
ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን እየተኩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ቶን ምርት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት መተካት ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ለውጭ ምንዛሬ ይውል የነበረውን ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ውጪ ማስቀረት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡ ይህም ታላቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡ የተገኘው ስኬት ሰላም በተጠናከረ ቁጥር የኢንቨስትመንት ፍሰቱም በእጅጉ እንደሚጨምር ማሳያ መኾኑንም አንስተዋል፡፡
በአማራ ክልል በበዓመቱ መጀመሪያ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ገደማ ሥራ ፈላጊ ዜጎችን ተመዝግበው ለ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች በቋሚነት እና በጊዚያዊነት የሥራ እድል መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡ ይህም የእቅዱን 91 በመቶ መፈጸም መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ልማት በተፈጠረ ቁጥር የሥራ እድልም በስፋት እየተፈጠረ ይሄዳል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ በማዕድን ዘርፍም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን የተናገሩት አቶ ግዛቸው ክልሉ ያሉትን ጸጋዎች የሚለይ ፍኖተ ካርታ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ ክልሉ የከበሩ ማዕድት መገኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የሲሚንቶ ችግርን ለመቅረፍ የሚረዱ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ክልሉ በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ ሳይኾን በማኅበራዊ ዘርፉም ከፍተኛ ሥራዎችን መሥራቱን አስታውቀዋል፡፡ በትምህርት ዘርፍ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አበረታች ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ በዓመቱ 124 ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል ብለዋል፡፡ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሳደግ ሥራ መሠራቱንም አስታውቀዋል፡፡ መንግሥት ልማትን ማረጋገጥ የሕልውና ጉዳይ ነው በማለት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በጤናው ዘርፍም በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት አቶ ግዛቸው 467 የሚኾኑ የጤና ፕሮጄክቶች እየተሠሩ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በጤና ሥርዓቱ ለውጥ ለማምጣት በስፋት እየተሠራ መኾኑንና ለውጥ መምጣቱትን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መሠረታዊ አጀንዳዎች ሰላምና ልማት መኾናቸውን ያነሱት አቶ ግዛቸው መላው ሕዝብ ለሰላም ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡ ልማት እንዲፋጠን የሃይማኖት ተቋማት፣ ወጣቶች እና መላው ሕዝብ ለሰላም በትኩረት መሥራት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን መግታት እና ልማትን ማፋጠን ግድ ይላልም ብለዋል፡፡ በልማቱ የተገኘው ውጤት በጦርነት ለኖረ ክልል በቀላሉ የሚታይ አለመኾኑንም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!