በበጀት ዓመቱ በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ከ510 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች ማጠናቀቁን መንገድ ቢሮ ገለጸ፡፡

20

ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ በትግሉ ተስፋሁን እንዳሉት በክልሉ የመንገድ ተደራሽነትንና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በሁሉም ዞኖች የመንገድ ግንባታ እያከናወነ ይገኛል፡፡

በ2015 በጀት ዓመት ለመሥራት ከታሰቡት 111 የመንገድ ፕሮጀክቶች 74 ተጠናቅቀዋል፡፡ መንገዶቹ ደረጃ ሦስት የጠጠር መንገድ ሲኾኑ 512 ኪሎ ሜትር ርዝመት አላቸው፤ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብርም ወጭ ተደርጎባቸዋል፡፡

በክልሉ ባጋጠመው የሰላም ችግር፣ የግንባታ ዋጋ ማሻቀብ እና በግብዓት አቅርቦት ችግር የታቀዱ ፕሮጀክቶች እንዳይጠናቀቁ እና ለአንዳንድ ፕሮጀክቶችም መጓተት በምክንያትነት ተነስቷል፡፡ ከግብዓት አቅርቦት ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት በአንድ ማዕከል ይፈጸም የነበረውን የግብዓት ግዥ በእያንዳንዱ ፕሮጀክት በኩል እንዲፈጸም በማድረግ ችግሩን ማቃለል መቻሉን አንስተዋል፡፡ በቀጣይ በጀት ዓመትም ለተጓተቱት ፕሮጀክቶች ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በ2015 በጀት ዓመት በክልሉ በፌዴራል እና በክልል መንግሥት እንዲሁም በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በተሰበሰበ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መንገድና ተያያዥ ሥራዎች ማከናወን ተችሏል ብለዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ፡-
👉በፌዴራል መንግሥት በተመደበ ከ378 ሚሊዮን 254 ሺህ ብር በላይ በጀት 200 መንገዶች የጥገና ሥራ ተሠርቷል፡፡

👉በማኅበረሰቡ ተሳትፎ እና ከወረዳዎች በተሰበሰበ 1 ቢሊዮን ብር 187 ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል፡፡

👉43 ድልድዮች ተጠናቅቀዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 21 ተንጠልጣይ ሲኾኑ ቀሪዎቹ የኮንክሪት ድልድዮች ናቸው፡፡

👉 ከ 520 በላይ ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ 14 የመንገድ ፕሮጀክቶች ደግሞ የዲዛይን ሥራ ተጠናቅቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበግብይት ሥርዓቱ ላይ ያለው ሕገ ወጥነት ጫናው የሚያርፈው ኀብረተሰቡ በመኾኑ ዜጎች ለሕገ ወጥ ንግድና ሥራ ባለመተባበር ችግሩን ለመከላከል እንዲሠሩ ጥሪ ቀረበ።
Next article“በአማራ ክልል ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ