
ደብረ ታቦር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኑሮ ውድነትና ሕገ ወጥ ንግድ እየተመጋገቡ በኀብረተሰቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ባላቸው የኀብረተሰብ ክፍሎች ላይ ኑሮን እንዳከበዱት በዕለት ከዕለት እየታየ ነው፡፡
ችግሩን ለመፍታት በክልልና በዞን የሥራ ኀላፊዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራት እንዳለበት ተወስኖ የ5 ወራት እቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ለዚህም ከክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ተቋማትና አጋር አካላት በተናጠልና በጥምረት ኮሚቴዎችና አሠራሮች ዘርግተው ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ሥራው ከተጀመረ 2 ወራት ኾኖታል። ሥራው ያለበትን ደረጃ፤ ምን ውጤት እንዳስመዘገበና ምን መስተካከል እንዳለበት የሚገመግም ውይይት በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አዘጋጅነት ተካሂዷል፡፡
በውይይቱ ዞኖችና ወረዳዎች፣ እንዲሁም ለችግሩ እልባት ለመስጠት ቅርበትና ኀላፊነት ያለባቸው ተቋማት በተናጠልና በጋራ የሠሯቸው ሥራዎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ዞኖችም ሌሎች ይማሩበት ዘንድ ተሞክሯቸውን አቅርበዋል፡፡ ሌሎች ዞኖችም የሠሯቸውንና ያጋጠሙ ችግሮች ተነስተው በመፍትሔያቸው ላይም ውይይት አድርገዋል፡፡
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ አሸናፊ ደረሰ በዞኑ የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ከዩኒየኖችና ከኀብረት ሥራ ማኀበራት ጋር በመተባበር 15 ሺህ ኩንታል የግብርና ምርት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች ማቅረባቸውን ገልጸዋል። የዱቤ አቅርቦት እንደተፈጸመና ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል በቁርጠኝነት እየተሠራ መኾኑን መምሪያ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪይ ኀላፊ ቴዎድሮስ ጸጋየ የኑሮ ውድነትንና ሕገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ለገበያ ለማረጋጋት እስከ 50 ሚሊዮን ብር ድረስ በጀት መመደቡን ተናግረዋል። ከክልሉ ውጪ ጭምር ባሉ አካባቢዎች የግብይት ትሥሥር ተፈጥሮ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ነዋሪዎች መሠረታዊ ሸቀጦች እየቀረቡ ነው ብለዋል፡፡ ከራስ ደጀን ዩኒየን ጋር በመግባባት ለመንግሥት ሠራተኛው እስከ 100 ኪሎ ግራም ጤፍ በዱቤ እየተሰጠ መኾኑንም አብራርተዋል፡፡
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የመርከብ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ ጌታቸው እሸቴ ዩኒየኑ ትርፍን ሳይሻ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ መኾነን ነው የተናገሩት፡፡
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኀላፊ ዶክተር ኢብራሂም መሐመድ ከ2 ወራት በፊት የክልልና የዞን የሥራ ኀላፊዎች የዋጋ ግሽበትና ኑሮ ውድነቱ ኀብረተሰቡን ስላማረረው ችግሩን የሚፈታ የንቅናቄ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ኀብረተሰቡ ላይ ችግር እያደረሰ ስለኾነ ከጅምላ ነጋዴው ጋር ጥብቅ ውይይት እያደረጉ መኾኑን ነው የገለጹት። ዶክተር ኢብራሂም ጎንደርና ደብረማርቆስ ከተሞች፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ጎንደርና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች ጥሩ ጅምሮች እንዳሏቸው ታይቷል ብለዋል፡፡ በአንጻሩ የተሻለ እንቅስቃሴ ያላደረጉ አካባቢዎች ደግሞ በቅርብ ኪሎ ሜትር በቅናሽ ዋጋ የሚሸጥ ምርትን በትስስር ማቅረብ ባለመቻላቸው የኑሮ ውድነቱ ሲያስቸግራቸው መታየቱን ተናግረዋል ።
የኑሮ ውድነትን ለመከላከል እንቅፋት ከነበሩት መካከልም ምርት የሚገዛበትና ሚጓጓዝበት ካፒታል መጥፋቱ አንዱ እንደነበር ቢሮ ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍም ወረዳዎች፣ ዞኖችና ዩኒየኖች በሰጡት ብድር 414 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦ ወደሥራ መገባቱን ጠቅሰዋል፡፡
የኑሮ ውድነትን ለመከላከል ትኩረት ከተሰጠባቸው ውስጥ አንዱ ሕገ ወጥ ደላላን መከላከል መኾኑ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ”የእሁድ ገበያ” በመባል የሚጠሩ አምራችና ሸማች ደላላ ሳይገባባቸው በቀጥታ የሚገናኙባቸውን ቦታዎችና ጊዜ ወስኖ በማብዛት በኩልም ከሁለት ወራት በፊት በክልሉ ከነበሩት 32 ”የእሁድ ገበያዎች” አሁን ላይ ወደ 79 ማሳደግ ተችሏል።
ምንም እሴት ሳይጨምር በግብይት መሃል እየገባ በሸማቹ ላይ ችግር የሚፈጥርን ደላላ ለመከላከል አሠራር ቢበጅም አሁንም ድረስ ችግሩ በበቂ ኹኔታ አለመቀረፉን ዶክተር ኢብራሂም ተናግረዋል፡፡ በግብርና እና በእንስሳት ምርት ላይ የድለላ ፈቃድን የፌዴራል መንግሥት ቢሰርዘውም አሁንም ችግሩ አለመቀረፉን ኀላፊው ጠቅሰዋል፡፡
ከአቅራቢዎች ጋር ውይይት በማድረግ ፍትሐዊ የንግድ ሥርዓት እንዲከተሉ ማድረግ፤ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎችን ማጠናከር፤ ምርት ካለበት ወደሌለበት አካባቢ የምርት ትስሰሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ፤ ሕገ ወጥነትን ታግሎ ማስተካከል በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው ብለዋል ዶክተር ኢብራሂም።
በንግድና በግብይት ሥርዓቱ ላይ ያለው ሕገ ወጥነት መልኩ ብዙ ቢኾንም ጫናው የሚያርፈው በኀብረተሰቡ ላይ ስለኾነና ችግሩም የሚፈጸመው በኀብረተሰቡ ውስጥ ስለኾነ ዜጎች ለሕገ ወጥ ንግድና ሥራ ባለመተባበር ችግሩን ለመከላከል እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ዋሴ ባየ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!