
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ልማት ማኅበር አልማ በየዓመቱ ከሐምሌ 1-15 የሚያከብረውን “የአልማ ሳምንት” በማስመልከት መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን የሰጡት የአልማ የሕዝብ ግንኙነት እና ተግባቦት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ሞገስ ማኅበሩ መንግሥታዊ ባልኾነ ድርጅት ሥም 800 በሚደርሱ የክልሉ በጎ አሳቢዎች በ1984 ዓ.ም እንደተመሰረተ አንስተዋል።
አማራ ልማት ማኅበር በሰላሳ ዓመት ጉዞው የክልሉን ሕዝብ አንገብጋቢ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉድለቶችን በመለየት እየሠራ የዘለቀ ተቋም ነው። በግብርና፣ በገጠር መንገድ ሥራ፣ የወጣቶች ክህሎት ስልጠና፣ ሥራ ፈጠራ፣ በትምህርት፣ በጤና እና በሌሎችም መስኮች ፋታ የማይሰጡ ችግሮችን መፍትሔ በመስጠት አጋርነቱን አሳይቷል ብለዋል አቶ አለማየሁ።
ከሀምሌ 1-15 በሚኖረው የ2015 የአልማ ሳምንት ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ ያጠናቀቃቸውን ፕሮጀክቶች ለተጠቃሚው ማኅበረሰብ የሚያስረክብበት ይኾናል ተብሏል። ሳምንቱ በሂደት ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች የሚጎበኙበት እና በጎ ፈቃደኞችን የሚያነቃቁ እንደ ደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላ፣ የሩጫ ውድድር እና መሰል ኹነቶች የሚካሄዱበት እንደሚኾንም አቶ አለማየሁ በመግለጫቸው አንስተዋል።
በማኅበሩ የሚሠሩ ግንባታዎች በጊዜ እና በጥራት እንዲከናዎኑ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት መከታተሉ እና ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ማድረጉ የዚህን ዓመት የአልማ ሳምንት ልዩ ያደርገዋል ሲሉ አቶ አለማየሁ ተናግረዋል። በተደረገው የሕዝብ ርብርብ ከመጋቢት 2015 ዓ.ም ወዲህ በተደረገው ርብርብ ብቻ 7 ሽህ 328 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተው ለአገልግሎት ዝግጁ መኾናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አልማ በተለይም ከ2012 ዓ.ም ወዲህ በፈጣን ለውጥ ላይ እንደሚገኝም በመግለጫው ተነስቷል። ማኅበሩ በተግባር ሂደት እየተማረ እና ልምድ እየቀሰመ በየጊዜው በማደግ ላይ የሚገኝ ነውም ብለዋል። ማኅበሩ የአባላቶቹንና የክልሉን መንግሥት የልማት ጥያቄ ክፍተት የመሙላት አቅሙን እያጎለበተ ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።
አልማ ለዘላቂ ልማት ሃብት የሚያመነጩ እና ለክልሉም ገጽታ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ እንደ ዋንዛየ ፍል ውኃ ሎጅ፣ ጢስ አባሊማ የንጹህ መጠጥ ውኃ ማሸግ እና በየዞኑ ባለ አስር ወለል ሕንፃዎችን የመገንባት ፕሮጀክቶችን ይፋ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
“አልማ መሰረቱን እያሰፋ፣ ሕዝባዊነቱን እያረጋገጠ ፕሮጀክቶቹንም በብቃት እየፈጸመ ነው”ሲሉ አቶ አለማየሁ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። እስካሁን ድረስ ከማኅበሩ ጎን ያሉ አባላት፣ ደጋፊዎች፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ አጋሮች በቀጣይነትም የሕዝብን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ አቶ አለማየሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!