
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ የክልሉ ጉዳይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም በግብርናው ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ክልሉ በፈተናዎችም ውስጥ ኾኖ በግብርናው ዘርፍ አበረታች ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡ ክልሉ በ2015/16 የምርት ዘመን 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 160 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት ማቀዱንም ገልጸዋል፡፡
የምርት ሥራው እንዲያድግ የእርሻ ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የአማራ ክልል በምርት ዘመኑ 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እንደሚፈልግ ያነሱት አቶ ግዛቸው ከገጠመው ዓለማቀፍ ሁኔታ እና ሌሎች ችግሮች አንጻር የተገዛው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
እስከ ሰኔ 27/2015 ዓ.ም ድረስ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ደግሞ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡ መዳበሪያው ዘግይቶ መግባቱንም አንስተዋል፡፡ መንግሥትም መዘግየቱን ለመፍታት እርብርብ ሲያደርግ መቆየቱን ነው የተናገሩት፡፡ የተገዛው ማዳበሪያ ያለ መቆራረጥ እየገባ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ከመዘግየቱም ባለፈ ወደ ክልሉ የገባውን ማዳበሪያ በሕገወጥነት የመጠቀም አዝማሚያ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ በሕገወጥ መንገድ በመውሰድ ዋጋ ጨምሮ የመሸጥ፣ መጋዝኖችን የመዝረፍ አዝማሚያዎች እንደነበሩ ያነሱት ኀላፊው ከጸጥታ አካላት ጋር በተሠራው ሥራ ያልተገቡ ዝንባሌዎችን መግታት ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የአፈር ማዳበሪያ እጥረቱን ለመቅረፍ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በሥፋት የመጠቀም ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ግዢ የተፈጸመው ማደበሪያ በቀሪ ጊዜያት ወደ አርሶ አደሩ እንደሚደርስም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ ይታረሳል ተብሎ ከተያዘው 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚኾነው በዘር መሸፈኑንም አንስተዋል፡፡ የተገዛው ማዳበሪያ ለቀሪው ዘር በፍጥነት ይጓጓዛል ነው ያሉት፡፡
በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር የተሻሻሉ ምርጥ ዘሮች እየቀረቡ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ በክልሉ የምርጥ ዘር ችግር አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የደን ልማት ሥራ በስፋት እየተሠራበት መኾኑንም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!