የአማራ ክልል በፈተናዎች ውስጥ ኾኖም በርካታ የልማት ሥራዎችን መሥራቱን አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ተናገሩ፡፡

34

ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል በፈተናዎች ውስጥ ኾኖም በርካታ የልማት ሥራዎችን መሥራቱን አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኀላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት መግለጫ የአማራ ክልል ሰላምን የሚያውኩ ተግዳሮቶች የበዙበት፣ እሳት ማጥፋት ላይ የመጠመድ አደጋ የገጠመው ክልል ቢኾንም በዓመቱ ታላላቅ ፕሮጄክቶችን መሥራቱን ገልጸዋል፡፡

በአማራ ክልል በመንገድ ጥገና፣ በዲዛይን እና በመንገድ ግንባታ 541 ፕሮጄክቶች በዓመቱ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ታቅዶ 500 ፕሮጄክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል ነው ያሉት፡፡ የተሠራው ሥራም ስኬታማ እንደኾነ አንስተዋል። ከሕዝቡ፣ ከክልሉ ማንግሥትና ከፌዴራል መንግሥት በተገኘው በጀት የተሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ፕሮጄክቶቹ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው እንደኾኑም አንስተዋል፡፡

በዓመቱ 122 የመስኖ ፕሮጄክቶችን ለማጠናቀቅ ታቅዶ እስከ 11ኛው ወር ድረስ 56 ፕሮጄክቶችን ማጠናቀቅ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡ 57 መካከለኛ የመስኖ ፕሮጄክቶችም የጥናት ዲዛይን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነውም ብለዋል፡፡ የጥናት ዲዛይናቸው የተጠናቀቁ መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ እየተገነቡ ያሉ አምስት ታላላቅ የመስኖ ፕሮጄክቶች በጥሩ አፈጻጸም ላይ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን ታላላቅ የልማት ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡

በከተማ ልማት ዘርፍ ታላላቅ ሥራዎች መሠራታቸውን የተናገሩት ኀላፊው የዓለም ባንክ የሚሠራቸውን ሳይጨምር በሕዝብ ተሳትፎ ብቻ 848 ፕሮጄክቶች ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎባቸው ተሠርተዋል ነው ያሉት፡፡ በሕዝብ ተሳትፎ የተሠሩት ፕሮጄክቶች የአማራ ክልል ሕዝብ ምን ያክል ልማት ወዳድ ሕዝብ መኾኑን ያሳዩ ናቸውም ብለዋል፡፡ በዓለም ባንክ በታቀፉ ከተሞችም በርካታ ፕሮጄክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል ነው ያሉት፡፡

የንፁሕ መጠጥ ውኃ ተደራሽነትን ከፍ ለማድረግ አበረታች ሥራ መሠራቱን የገለጹት ኀላፊው 1 ሺህ 358 አነሰተኛ እና 10 ከፍተኛ የንጹሕ መጠጥ ውኃ በገጠር፣ በከተሞች ደግሞ 8 ታላላቅ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፕሮጄክቶች መሠራታቸውንም አንሰተዋል፡፡

በኢነርጂ ዘርፍም በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ያነሱት አቶ ግዛቸው 1 ሺህ 845 የባዮ ጋዝ ማብላያዎችን በመገንባት በሺዎች የሚቆጠሩ የቤተሰብ አባላትን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡ ይህም ሥራ ክልሉን በሀገር አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሁለተኛው ምዕራፍ የመጀመሪያ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ አብጠራ ቀበሌ እየተካሄደ ነው።
Next article“3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ አማራ ክልል ገብቷል” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ