
ደባርቅ: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ፕሮግራሙ ” ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት እየተካሄደ ነው። በአረንጓዴ አሻራ መረሐ ግብሩ ላይ የፌደራል እና የክልል የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። በመርሐ ግብሩ በዳባት ወረዳ የተጠለሉ የኤርትራ ስደተኞች ተሳትፈዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኀይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) በክልሉ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል፤ እስካሁን ድረስ ግማሽ ቢሊዮን ችግኝ መተከሉን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት በተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ6 ቢሊዮን በላይ ችግኞች በ7 መቶ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መተከላቸውንም ተናግረዋል። ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዳባት ወረዳ አብጠራር ቀበሌ ተካሂዷል። መርሐ ግብሩ ጀግኖች ወንድሞቻችን የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማስታወስ እና የልማት ጀግና በመኾን በምግብ ራስን ለመቻል ችግኝ መተከሉ አስፈላጊ ነው ብለዋል ቢሮ ሃላፊው።
ዶክተር ኃይለማርያም የተተከሉ ችግኞች ምግብ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ችግኞች ጸድቀው የአካባቢውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንዲረዱ እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል። የአፈር እና ውኃ ጥበቃ በየዓመቱ መሠራቱ የደን ሽፋናችን ጨምሯል፣ የአፈር ክለትንም 22 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በአሲድ የተጠቃ ሲኾን ከ6መቶ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከጥቅም ውጭ ኾኖ መቆየቱንም ተናግረዋል። አሲዳማነትን ለማከም አረንጓዴ አሻራ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል የሚሉት ቢሮ ኃላፊው ሁሉም በኀላፊነት ስሜት ችግኞችን እንዲተክል እና እንዲንከባከብ አሳስበዋል።
ቢሮ ኅላፊው የከርሰ ምድር እና የገጸምድር ውኃ እንደጨመረም ጠቁመዋል። ምርታማነትን በማሳደግ በኩል ድርሻው ከፍተኛ ነው ያሉት ኀላፊው የተተከሉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ዛፎች ፍሬ እንዲያፈሩ እና የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ በኩልም ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የስደተኞች ተፅዕኖ ምላሽ ልማት ፕሮጀክት ማናጀር ንጋቱ ቦጋለ በበኩላቸው ስደተኞች በሚገኙበት አካባቢ መተከሉ የአካባቢ መራቆትን ለመከላከል ይረዳል ብለዋል። የጃምበሎ ቀበሌ ግብርና አስተባባሪ ዛየደ አየልኝ በበኩላቸው ቦታውን ከሰዎች እና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ የጽድቀት መጠኑን መቶ ፐርሰንት ለማድረስ እየሠሩ መኾኑን ነግረውናል።
የታላቅ መስክ ቀበሌ የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ ሃብቴ ማለደ እንደተናገሩት ችግኞችን ተግተን እየተከልን ነው ችግኝኞችን ከመትከል ባሻገር ለመንከባከብም ዝግጁ ነን ብለዋል።
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!