“የግል ትምህርት ቤቶች ከትርፍ ባሻገር ሚናቸውን በልኩ መወጣት አለባቸው” ዶክተር ማተብ ታፈረ

48

ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የግል ትምህርት ቤቶች ማኅበር በባሕር ዳር ከተማ የትምህርት ዓውደ ጥናት እያካሄደ ነው። ዓውደ ጥናቱ “የግል ትምህርት ቤቶች አበርክቶ፣ ተግዳሮትና መፍቻ መንገዶች” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው፡፡

በዓውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ማተብ ታፈረ (ዶ.ር) እንደ ሀገር ያጋጠመውን የትምህርት ሥብራት ለመጠገን ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚገባውም ተናግረዋል። በትምህርት፣ በዕውቀት ዘመኑን የዋጀ ትውልድ መገንባት እንዲቻልና የተሠበረው የትምህርት ሥርዓት እንዲጠገን የግል ትምህርት ቤቶች ከትርፍ ባሻገር ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።

የግል ትምህርት ቤቶች በሀገር ግንባታው ቁልፍ ሚና አላቸው ያሉት ዶክተር ማተብ የነገ ሀገር ተረካቢ፣ ሀገር መሪና ሀገር አሻጋሪ ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችል ተግባር ላይ የተሰማሩ ናቸውና ይላሉ። ሀገር የሚገነባው በትውልድ ነው፤ ጠንካራ መንግሥት ለማንበር፣ ጠንካራ ሞጋች ፓርቲ ለመፍጠር፣ ጠንካራና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን በሀገር እውን ለማድረግ የትምህርት ዘርፍ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ነው የሚሉት።

ዶክተር ማተብ በመድረኩ እንደተናገሩት ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት የገነቡ ሀገራት ናቸው ሀገራቸውን እንደሚፈልጉት ያሻገሩት፣ ወደ ላቀ ዝምንናም የደረሱት። ዶክተር ማተብ ችግሮችን በውይይት መፍታትና ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ መውለድ የሚችል ዜጋ መፍጠር የሚቻለው በትምህርት መሆኑን አንስተዋል። የትምህርት ዘርፉ ከስብራቱ እንዲላቀቅ የሚያስችል ጥናት ተደርጎ የአሥር ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷልም ብለዋል፡፡

በጥናት ማረጋገጥ እንደተቻለው የትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች መኾን፣ የመምህራን ልማት ችግር፣ የመማር ማስተማር ባሕል ሥብራት፣ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ አለመጠቀም ችግር የትምህርት ዘርፉ ስብራቶች ስለመኾናቸውም አስገንዝበዋል፡፡

መንግሥት ሥብራቶችን ለመጠገን እየሠራ ነው የሚሉት ቢሮ ኀላፊው ችግሩ በአንድ አካል ብቻ የሚታከም አይደለምና ለልጆቻችን ጥሩ ሀገር፣ ጥሩ ሥርዓት ማስቀመጥና ማስረከብ ከፈለግን ትምህርት ላይ ያለውን ሥብራት ተባብረን እንጠግን፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኀላፊነቱን ይወጣ ሲሉ አሳስበዋል። በግል ትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን ተግዳሮት ለመፍታት እና ሚናቸውንም በልኩ እንዲወጡ ለማስቻል መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል፣ ኀላፊነቱንም ይወጣል ነው ያሉት።

ዘጋቢ:-ጋሻው አደመ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ምቹና አስተማማኝ ሥራ ለአፍሪካ ብልፅግና ” በሚል መሪ ሃሳብ የመጀመሪያው የአፍሪካ የሥራ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።
Next articleጤና ሚኒስቴር ለአገልግሎት ምቹና ቀላል የኾነ ድጅታል የክፍያ ሥርዓትን እያስተዋወቀ ነው።