“የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚመለሰው ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ነው” አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

47

ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ግዛቸው ሙሉነህ በወቅታዊ ጉዳዮች መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸው ዘላቂ ሰላምን እና የልማት ጉዳዮችን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ አተኩረዋል።
ዘላቂ ሰላም ለአማራ ሕዝብ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል። ዘላቂ ሰላም እና ልማት የማይነጣጠሉ ፣ የክልሉ ሕዝብ በጥብቅ የሚፍልጋቸው እና የሚያስፈልጉት ናቸው ብለዋል። ፀጋውን ለመጠቀም ሰላም ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአብዛኛው የክልሉ አካባቢ ልማት የሚካሄድበት ሰላማዊ ቢኾንም በየጊዜው የሚዋዥቅ የሰላም ችግር የሚገጥመው ክልል መሆኑንም አስታውሰዋል። በክልሉ የሆነውን በልኩ መግለፅ ተገቢ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው ያልሆነውን ደግሞ አግዝፎና አንሻፎ መግለጽ ተገቢ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

ክልሉ ችግር የሚፈራረቅበትና የሚሰጡ አጀንዳዎች የሚያርፉበት መሆኑንም ገልጸዋል። የአማራ ክልል ከነበረው ጦርነት ጫና ያልተላቀቀ መሆኑንም አንስተዋል። በጦርነቱ ምክንያት የሥነልቦና ጫና ያለበት፣ መፈናቀል ፣ ከቦታ ቦታ በሰላም የመንቀሳቀስ ችግር ፣ ሞትና አደጋ ያለበትና የሰላም እጦት እና ጫና ያለበት ክልል ነውም ብለዋል። ለሰላም እጦቱ ምክንያት ውጫዊ እና ውስጣዊ ጫናዎች መሆናቸውንም አስታውቀዋል። በንግግር መፍታት እየተቻለ አካል የሚጎድልበት፣ ነብስ የሚጠፋበት ሂደት እንዳለም ገልጸዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች ጥሩ ያልሆነ አካሄድና እንቅስቃሴ መኖሩንም ተናግረዋል። የሰላም እጦት ሲኖር በተፈለገው ልክ መልማት እንደማይቻልም ገልጸዋል። የተጀመሩ ፕሮጀክቶችም ይስተጓጎላሉ ስራ አጥነትም እየሰፋ ይሄዳል ነው ያሉት። የሰላም እጦት ሲኖር የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብስና ሕዝብን እንደሚጎዳ ነው የተናገሩት። ይህ ሁኔታም የክልሉን ሕዝብ በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ ክልሉን ሰላማዊ ለማድረግ ሁሉም ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት።

እነዚህ ችግሮች አማራን እንደ ሕዝብ የሚያዋርዱ፣ የበለጠ ችግሮችን እያወሳሰቡ የሚሄዱና ወደ ኋላ የሚያስቀሩ መሆናቸውንም አንስተዋል። የአማራ ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉበት ያነሱት ኃላፊው ጥያቄዎችን ለማስመለስ ሰላማዊ ትግል እና የውስጥ አንድነት ያስፈልጋል ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚመለሰው ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ፣ በወንድማማችነት እና በእህታማማችነት ላይ በመመስረት፣ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ሆኖ በብልህነት ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

ክልሉ በአብዛኛው ሰላማዊ ቢሆንም አደገኛ ምልክቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል። ሕግ መከበር መቻል አለበትም ብለዋል። ያልተገባ አካሄድ የክልሉን ሕዝብ ይጎዳል እንጂ ሌላ ጥቅም የለውም ነው ያሉት አቶ ግዛቸው።

ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሂጅራ ባንክ የሀብት መጠኑ 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገለጸ።
Next article“ምቹና አስተማማኝ ሥራ ለአፍሪካ ብልፅግና ” በሚል መሪ ሃሳብ የመጀመሪያው የአፍሪካ የሥራ ጉባዔ እየተካሄደ ነው።