
ባሕር ዳር: ሰኔ 30/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ሂጅራ ባንክ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በ2022/2023 በጀት ዓመት የሃብት ምጣኔውን 207 በመቶ በማሳደግ 7 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን ገልጿል።
የሂጅራ ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ አብዱሰላም ከማል ባንኩ ይህንን ስኬት ማምጣት የቻለው በኢንዱስትሪው ከፍተኛ ውድድር በሚስተዋልበት ወቅት መኾኑ ስኬቱን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል ብለዋል፡፡ ሂጅራ ባንክ በ2022/2023 በጀት ዓመት 162 በመቶ የጥቅል ትርፍ መጠኑን ማሳደጉንም አስገንዝበዋል።
ሂጅራ ባንክ ይህንን ስኬት ያስመዘገበው በሀገሪቱ በወለድ ነጻ ባንክ ዘርፍ ውጤታማ ለመኾን በተከለው የኢንቨስትመንት አማራጭ መኾኑን የተናገሩት የቦርድ ሰብሳቢው በአምስት ዓመት ለማሳካት የተያዘው ስትራቴጂካዊ እቅድ አካል ነው ብለዋል።
እንደ ቦርድ ሰብሳቢው ገለጻ፡-
👉 ባንኩ የደንበኞች ብዛት ማሳደግ ላይ 122 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡
👉 የቅርንጫፍ ብዛቱን ወደ 80 በመቶ ማሳደግ ችሏል።
👉 የባንኩን ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 273 በመቶ አሳድጓል።
👉 ዓመታዊ ገቢውን ወደ 1ሺህ 442 በመቶ ማሳደግ ችሏል።
👉 ሙሉ ለሙሉ የወለድ ነጻ ባንኮችን ብቻ ታሳቢ ተድርጎ የበለፀገ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሸሪዓ መርሕ ሙሉ በሙሉ የተመጣጠነ ቴክኖሎጂ እየተጠቀመ ያለ ባንክም ነው።
👉 ከ165 በላይ የኾኑ የዓለማችን ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች የሚገለገሉበትን የአይማል ኮር ባንኪንግ ሲስተም በአጭር ጊዜ ሥራ ላይ ማዋል የቻለም ነው ብለዋል።
የባንኩ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ በበኩላቸው ሁሉንም ማኅበረሰብ ያሳተፈ የፋይናንስ ሥርዓት በኢትዮጵያ እንዲዘረጋ መደረጉ ሂጅራ ባንክንና ደንበኞችን ተጠቃሚ እንዳደረገ ገልጸዋል። ባንኩ በኢኮኖሚ ላይ ጠንካራ ተወዳዳሪ እና ብቁ ለመኾን እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ድርሻውን ለመወጣት ይተጋል ነው ያሉት። ኡስታዝ አቡበክር ብሔራዊ ባንክን ለእስካሁኑ ድጋፍ አመሥግነው በቀጣይም ለባንኩ ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ሂጅራ ባንክ በቀጣይ በጀት ዓመት ተጨማሪ አዳዲስ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ እስካሁን ሲሰጣቸው ከነበሩት የወለድ ነጻ አገልግሎቶች በተጨማሪ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርግ ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ዘጋቢ፡- ዳንኤል መላኩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!