አገልግሎት አሰጣጡ ለብልሹ አሠራር እንዲጋለጥ መንስኤ ሆነዋል ያላቸውን ሠራተኞቹን ከሥራ ማገዱን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

75

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግስትና የሕዝብን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ከተቀመጠው አሠራር ውጪ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ብልሹ አሠራር እንዲፈጠር መንስኤ ሆነዋል ያላቸውን ሠራተኞቹ ከሥራ ታግደው ጉዳያቸው እንዲጣራ ውሳኔ ማሳለፉን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የመንግስትና የሕዝብን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ፤ ለዜጐች ምቹ እና ከሙስና የፀዳ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ለመዘርጋት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑ ገልጿል፡፡ በዚህም የኦፐሬተር ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተደረገ ምርመራ፤ የሚኒስቴሩ 6 ሠራተኞች ከአሠራር ውጪ አገልግሎት ሲሰጡ በመገኘታቸው ለሚመለከታቸው የህግ ተቋማት ሪፖርት በማድረግ ተጨማሪ ምርመራዎች እንዲከናወኑ ውሳኔ መተላለፉ ነው የተገለጸው፡፡

የምርመራ ሪፖርቱ ከመመሪያ፣ ከመረጃ ህጋዊነት እና ከአሰራር ስርዓት አንፃር በርካታ ግኝቶችን ያመላከተ መሆኑ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ትክክለኛ ያልሆነ ሊብሬ በማያያዝ የኦፕሬተርነት ፈቃድ መስጠት፣ በተሳሳተ የተሽከርካሪ መረጃ ያለአግባብ የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት መስጠት፣ የአገልግሎት መስጫ አይቲኤም ኤስ ሲስተም ማሳሳት፣ ተሸከርካሪዎች የሌላቸውን የጭነት መጠን እንዳላቸው አርጐ በኦፐሬተር ፍቃዱ ላይ መስጠት፣ የግል ንግድ ተሽከርካሪዎችን እንደ ንግድ ተሽከርካሪ አካቶ ማደራጀት ተጠቃሾች ናቸው ተብሏል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬቱን አጽድቀው የሚሰጡ ኃላፊዎች፤ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው አገልግሎት አሰጣጡ ለብልሹ አሰራር እንዲጋለጥ መንስኤ መሆናቸውን የምርመራ ሪፖርቱ እንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በየደረጃው ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተሻግራ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ ችላለች” አቶ ደመቀ መኮንን
Next articleበሰሜን ጎንደር ዞን ምዕራብ ጠለምት ወረዳ ለዘንድሮው የችግኝ ተከላ ከ500 ሺህ በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለጸ፡፡