
ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ለአሚኮ በሰጠው መረጃ የገቢ ግብር አሰባሰብ ሥራ ላይ ሕገ ወጥነት እንደ ሀገርም ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰ፣መንግሥትና ሕዝብንም እየጎዳ ነው ብሏል።
እናም በክልሉ በገቢ ግብር ላይ የሚስተዋለውን የሕገ ወጥነት ፈተና ለመመከት የሚያስችል እርምጃ እየተወሰደ ስለመኾኑ ነው በቢሮው የግብር ፣ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አግማስ ጫኔ ለአሚኮ ኦንላይን የተናገሩት።
በተለይም ሐሰተኛ የገቢ ደረሰኝ በሚያዘጋጁና ደረሰኝ በማይቆርጡ ነጋዴዎች ላይ አስተማሪ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ባለፉት 10 ወራት በ1 ሺህ 418 ግብር ከፋዮች ላይ በተደረገ የሐሰተኛ ደረሰኝ ምርምራ 3 ሺህ 153 ሐሰተኛ ደረሰኞችን በማጣራት ማጋለጥ ተችሏል ብለዋል።
ከዚህም ከ814 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል ነው ያሉት አቶ አግማስ፡፡ በበጀት ዓመቱ የገቢ ግብር አሰባሰብ ላይ ፈተና ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ በግብይት ወቅት ደረሰኝ አለመቁረጥ እንደነበርም ነው አቶ አግማስ ያስረዱት።
ሕገ ወጥ ነጋዴዎቹ በተደጋጋሚ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ሊሻሻሉ ባልቻሉ 1 ሺህ 561 ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል። በዚህም የ50 ሺህ ብር አሥተዳደራዊ ቅጣት እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡
በተለይም በ47 ግብር ከፋዮች ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽን በመሥራት ለሕግ እንዲቀርቡ ተደርጓል ያሉት አቶ አግማስ 155 የወንጀል ጉዳዮችን፣ 97 የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን ለፍርድ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል። ወደ ፍርድ ቤት ከቀረቡ ጉዳዮችም 86 ግለሰቦች ከ6 ወር እስከ 8 ዓመት የእስራትና 573 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።
በተወሰደው የፍትሐብሔር ክስ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ መቻሉን ነው የተናገሩት። አቶ አግማስ በተለይም በሕገ ወጥ መንገድ የተሰወረን የገቢ ግብር በማስመለስ ረገድ የኀብረተሰቡ ተሳትፎ የሚመሰገን ነው ብለዋል።
በሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ዙሪያ ባለፉት 10 ወራት 598 ጥቆማዎች በኅብረተሰቡ ቀርቧል ያሉት አቶ አግማስ ቢሮው የደረሰውን ጥቆማ ሲያጣራ 553 ጥቆማዎች ትክክለኛ ኾነው ተገኝቷል ብለዋል። በእነዚህ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ በተወሰደ እርምጃም 107 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ዜጋ “የገቢ ግብርን በታማኝነት አለመክፈል ሀገርን መስረቅ ነው” የሚለውን መረዳት ይገባዋል ብለዋል።
ኅብረተሰቡ ግብይት ሲፈጽም ደረሰኝ የመጠየቅ መብትም፣ ግዴታም መኾኑን ተረድቶ ሕግን የማክበርና ማስከበር ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ነው የሚሉት አቶ አግማስ። በተለይም ደረሰኝ የማይሰጡ ነጋዴዎችን፣ ሐሰተኛ ደረሰኞችን ማጋለጥ፣ ለገቢዎች መሥሪያ ቤት በተዋረድ ጥቆማዎችን የማድረስ ጉዳይ ላይ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ነው የተናገሩት።
ከሕገ ወጥ ንግድ ጋር በተያያዘ በስልክ ጥቆማ ለማድረስ ለሚፈልጉ አካላትም 9504 የሥልክ መስመርን ተጠቅሞ መደወል እንደሚቻል ነው ቢሮው ያስታወቀው።
ሐሰተኛ ደረሰኝ ማዘጋጀት፣የገቢ ደረሰኝ አለመቁረጥ ፣የግብር ስወራና ማሸሽ ክልሉን ከፍተኛ ገቢ እያሳጣው ነው ያሉት አቶ አግማስ ሕገ ወጦችን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በማጋለጥ፣በመታገል የዜግነት ድርሻን መወጣት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ጋሻው አደመ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!