“የዋህ ዜጎች፣ ሌባ ደላሎች እና ነጋዴ ሹመኞች የፈጠሩትን ሕገ-ወጥ ድርጊት ለማረም ተስማምተናል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

61

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አሁናዊቷ ኢትዮጵያ ፈተና ብቻ ሳይኾን እድሎችም አሏት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፈተናዎቻችን አሁን ላለን ጠንካራ አሠራር ምንጭ ኾነው አግዘውናል ብለዋል፡፡

መንግሥት በርካታ ችግሮች አጋጥመውት ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮቹን በብስለት፣ በትዕግስት እና በቁርጠኝነት እየሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡ የሀገሪቱ ወቅታዊ ችግሮች ከሁለት ምንጮች ይቀዳሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእኔ ሃሳብ ብቻ ይደመጥ የሚሉ ፖለቲከኞች መኖር እና የወል እውነት ማጣት ለሀገራዊ ፈተናዎቻችን መሠረት ናቸው ብለዋል፡፡ ሁሉንም ችግሮች በስክነት እና በትዕግስት መመርመር ይገባል ብለዋል፡፡ ሀገራዊ አንድነት የሚመነጨው ከፍቅር እንጂ ከጥላቻ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍቅር ሳይኾን በጥላቻ መሰባሰብ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡

ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ኃይሎች የሕዝብ ጠላት የሚኾኑበት ምክንያት እርስ በእርሱ የሚምታታ መኾኑ በአንጻሩ መመልከት ይገባል “ከአንድ ደመና ሁለት መብረቅ አይወጣም” ለሕዝብ ቆሜያለሁ እያሉ ሕዝብን አቁሞ መዝረፍ ተገቢ አይደለም ፤ሊታረም ይገባል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ለሚስተዋሉ የቤቶች መፍረስ ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕገ-ወጥነት የተፈጠረው በተናበበ መንገድ ነው ብለዋል፡፡ “የዋህ ዜጎች፣ ሌባ ደላሎች እና ነጋዴ ሹመኞች የፈጠሩትን ሕገ-ወጥ ድርጊት ለማረም ተስማምተናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕግ ማስከበር ሂደቱ ችግሮች ካሉ ማስተካከል እና መካስ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡በቀጣይም እየተጣራ ክፍተቶች ይታረማሉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው፡፡

በችግር ውስጥ እድል፣ በነውጥ ውስጥ ለውጥ እና በውድቀት ወስጥ ስኬትን ማየት ከቻልን ኢትዮጵያ ያቀደቻቸውን ማሳካት ትችላለች፡፡ ነገር ግን ችግሮቹን ለማረም ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅ እና በጋራ የማደግ እድል እንደለ አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአግራ ኢትዮጵያ በግብርናዉ ዘርፍ እገዛ እንደሚያደርግ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአግራ የቦርድ ስብሳቢ ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
Next articleየ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀት 801 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ኾኖ በምክር ቤቱ ጸደቀ፡፡