
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 04/2012ዓ.ም (አብመድ) የፌዴራል ዕርቀ ሠላም ኮሚሽን አባላት ከአማራ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ተወያይተዋል፤ የውይይቱ ዓላማም ቀጣይ አብሮ መሥራት የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ነው፡፡
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እንዳሉት ለበርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ በተፈጠሩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች በሕዝብ ዘንድ ቁርሾዎች ታይተዋል፡፡ ዕርቀ ሠላም የሕዝብን ሠላምና ደኅንነት በዘላቂነት በማረጋገጥ የመንግሥትን የልማት ስትራቴጂ በጥራት እና በፍጥነት ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲሁም ዜጎች በመላ ሀገሪቱ ተንቀሳቅሰው በነጻነት እንዲሠሩ ምቹ ዕድል ይፈጥራልም ብለዋል፡፡ ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተልእኮ በአግባቡ እንዲወጣ ከየክልሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የኅብረተሰብ ተወካዮች ጋር ምክክር እያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ እንደ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ገለጻ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ፣ አዲስ አበባ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ ክልሎች ውይይት ተደርጓል፡፡
ዕርቀ ሠላም በባሕሪው አሳታፊ እና የችግርን መሠረት ነቅሎ በማውጣት ላይ ያተኮረ የግጭት መፍቻ ሂደት መሆኑን የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሎሬት የትነበርሽ ንጉሴ ተናግረዋል፡፡ ኮሚሽኑ የጋራ እውነት እንዲኖር፣ ለፍትሕ ሥርዓት አስተዋፅዖ ለማድረግ፣ ለተበዳዮች ዕውቅና ለመስጠት እና የባለፉ ግጭቶችን በማጤን ድጋሜ እንዳይከሰቱ የመከላከያ ርምጃ ለመውሰድ የጎላ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም ነው ሎሬት የትነበርሽ የተናገሩት፡፡
ዕርቀ ሠላም በአፍሪካ፣ በአውሮፓና አውስትራሊያ ሀገራትም ‹የአካባቢ ተወላጆች እና መጤ› ተብለው በሚጠሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም ተግባራዊ የተደረገ ሥነ ስርዓት መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ ‹‹የኮሚሽኑ ሥራ ውጤታማ እንዲሆን የክልሎችን ተባባሪነት ይጠይቃል›› ያሉት ሎሬት የትነበርሽ የአማራ ክልል ሕዝብና መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ኮሚሽኑ የሚያከናወናቸውን ተግባራት በቁርጠኝነት እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ላቀ አያሌው ‹‹አንዱ ቤተኛ ሌላው መጤ፣ ገዳይና ተገዳይ፣ አፈናቃይና ተፈናቃይ፣ በዳይና ተበዳይ፣ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ የመሆን አዝማሚያዎች በስፋት እየተስተዋሉ ነው›› ብለዋል፡፡ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የችግሩ ተጎጂ ቢሆኑም አማራ በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ ሆኖ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ኮሚሽኑ የችግሮችን ምንጭ በማጥናት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በሀገሪቱ ሠላም እና አንድነት እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ይኖረዋል›› ብለዋል አቶ ላቀ፡፡ ለኮሚሽኑ የክልሉ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ትብብር እንደማይለየውም ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የዕርቅ እና የሠላም መድረኮች እየተደረጉ መሆኑም ለዚህ አጋዥ እንደሚሆን አመላክተዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አካላት እንደተናገሩት እውነተኛ ዕርቀ ሠላም ቀጣይ ለሚፈጠረው ኢትዮጵያዊ አንድነት የማይተካ ሚና አለው፤ ነገር ግን ዕርቀ ሠላሙ በእውነት ላይ መመሥረት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ የተዛባ ትርክትን ማስተካከል እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
‹‹የችግሮች ምንጭ ታሪክ ነው›› ያሉት ተሳታፊዎቹ ዕርቀ ሠላም ውጤታማ እንዲሆን ትክክለኛውን ታሪክ መረዳት እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል፡፡ በሕዝብ ዘንድ ቅራኔ እንደሌለ በመግለጽም ልሂቃንን ማስተማር እና እራሳቸውን እንዲያሸንፉ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ በተለይ የውሸት ታሪክ እየፈጠሩ የጥላቻ ሃውልት ለማቆም የሚሠሩ አካላት ስላሉ መገሰጽ እና ወደ ቀልባቸው መመለስ እንደሚገባም ነው ተወያዮቹ የተናገሩት፡፡ መገናኛ ብዙኃን ሕዝብን ከሕዝብ ከሚያራርቁ አጀንዳዎች ወጣ ብለው ሕዝብን ከሕዝብ የሚያስተሳስሩ ዘገባዎች እንዲሠሩም ጠይቀዋል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ መስጠት እንደሚገባም ነው ተሳታፊዎች የተናገሩት፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ