
አዲስ አበባ: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሲስተም ኢንጅነሪንግ መጽሐፍ ምረቃ እና የሳታላይት መረጃን ተቀብሎ መተግበር የሚያስችል የ(ላሳክ) ፕሮጀክት ፕላትፎርም ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በስፔስ ሳይንስ እና ጅኦስፓሻል ኢንስቲትዩት አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው፡፡
የስፔስ ሳይንስ እና ጅኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ጠንካራ የመረጃ ሥርዓት አለመኖር ተግዳሮት መኾኑን አንስተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውና በምረቃ ላይ ያለው የሲስተም ኢንጅነሪንግ መጽሐፍ ጊዜና ወጪን ቆጣቢ፤ ከተለመደው የኘሮጀክት አሥተዳደር አካሄድ የተሻገረ፤ ክህሎት እና ቴክኒካል ብቃቱ ከመነሻው በየደረጃው የተተነተነበት ነው ብለዋል።
ተቋሙ ከቻይናው የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች መተግበሪያ ማዕከል (ላሳክ) ጋር በገባው ስምምነት መሠረት የበለጸገዉ የሳተላይት መረጃ መቀበያ ፕላትፎርም ሀገሪቱ በየዓመቱ ከሳተላይት ለምታገኛቸው መረጃዎች ታወጣ የነበረውን 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ የሚያስቀር መኾኑን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ ወደ ትግበራ ሲገባም የተራቆቱ አካባቢዎችን ለማልማት፣ ድርቅ፣ ጎርፍ እና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችን ቀድሞ ለመተንበይ ብሎም በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል ነው ተብሏል።
በመጽሐፉ ላይ የናሳውን ተመራማሪ መላክ ዘበናይን (ዶ.ር) ጨምሮ በርካታ መሐንዲሶች እንደተሳተፉበት ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ቤተልሄም ሰለሞን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!