
ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሰላም መጠናቀቅ እና የፕሪቶሪያው ሥምምነት በምን መልኩ እየሄደ ነው የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባለፉት ስድስት ወራት ለሰላም ከልባችን ሠርተናል ብለዋል፤ እንደዚያም ኾኖ አሁንም በርካታ የሚቀሩ የቤት ሥራዎች አሉ ብለዋል፡፡
ለሰላም ለመሥራት መቀራረብ እና ንግግርን ከማስተካከል ይጀምራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አካሄዶቻችን ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋግጡ እንዲኾኑ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ የተፈናቀሉትን መመለስ፣ የተጎዱትን መካስ እና የተቋረጠውን መልካም ተግባር መመለስ ያስፈልጋል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው፡፡
መመካከር፣ መደማመጥ፣ መከባበር እና መስከን ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ባለፉት 100 ዓመታት ከበቂ በላይ ጦርነት አድርጋለች፤ አሁን ሰላም አብዝታ የምትፈልግበት ወቅት ነው” ብለዋል፡፡
ድኀረ ጦርነት ከልብ መሥራትን እና ጠንካራ መኾንን ይጠይቃልና በትዕግስት እና በብርታት መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ አብሮ ለመኖር የሚያስችል የመቻቻል ባሕልን ማዳበር ፖለቲከኞቹ ከሕዝቡ ሊማሩ ይገባልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ወራት 370 ቶን የምግብ ድጋፍ በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች ደርሷል ብለዋል፡፡ በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተፈናቃዮች እንደነበሩ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው ተቋቁመዋል ብለዋል፡፡ ቀሪዎቹን ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቀያቸው ለመመለስ በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ተፈናቃዮችን በሚመለከትም በጊዜ ሂደት የተጠቂነት ስሜት እንዳይበረታ መሥራት ይገባል ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!