በሀገሪቱ ያሉ ችግሮችን መንግሥት እንዴት ሊፈታ እንዳሰበ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጠየቁ፡፡

48

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው፡፡ ምክር ቤቱ በመደበኛ ጉባዔው የመንግሥትን የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም እየገመገመ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

👉 የምክር ቤት አባላቱ በጥያቄያቸው የሀገሪቱ ዋና ዋና መንገዶች የስጋት ቀጣና መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
👉 በርካታ ዜጎች እየታገቱ እየተገደሉ ነው ያሉት የምክር ቤት አባላቱ ለማስለቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየተጠየቁ ነው፤ ይሄ እንዴት ነው የሚፈታው ሲሉም ጠይቀዋል?
👉 በአማራ ክልል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ምን አይነት ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል?
👉 በአዲስ አበባ ዙሪያ እየተካሄደ ባለው የቤት ፈረሳ፣ የግለሰቦች ቤት ብቻ ሳይኾን የሃይማኖት ተቋማት ፈርሰዋል፤ በዚህም ምክንያት ግጭት ተፈጥሮ የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ ሕገ ወጥ ቤት ሲሠራ መሪዎች የት ሄደው ነበር ? የሚሉት የምክር ቤቱ አባላት ተጠያቂነትስ አይሰፍንም ወይ? ቤት የፈረሰባቸው ግለሰቦች እና የሃይማኖት ተቋማት እጣ ፋንታስ ምንድን ነው? ሲሉ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
👉 በማኅበራዊ ሚደያ ላይ የሚተላለፉ የሐሰት እና የጥላቻ ንግግሮችን እንዴት መቆጣጠር እንደታሰበ የጠየቁት የምክር ቤቱ አባላት ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ምን እየተሠራ ነው? ሲሉ አንስተዋል
👉 እየተወሳሰቡ የሄዱት የሀገሪቱ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ችግሮች አሁን ላይ ወደ ቀውስ እየተሸጋገሩ ነው፤ ነጋዴው እንደ አሻው እንዳይነግድ፣ ገበሬው እንዳያርስ እየኾነ ነው፣ የኑሮ ውድነቱ ከአቅም በላይ ኾኗል፤ ሥራ አጥነት ተስፋፍቷል፣ ወጣቶች ተስፋ በማጣታቸው ስደትን አማራጭ አድርገዋል ብለዋል፡፡
👉 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖች የውስጥ ተፈናቃይ ኾነው በሰቀቀን እየኖሩ ነው ያሉት የምክር ቤቱ አባላት ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው መንግሥት ነው፤ በሀገሪቱ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ምን እየሠራ ነው? ሲሉ ጠይቀዋል
👉 የዜጎች መብት እየተከበረ አይደለም፣ ሕዝብ የሚያነሳው ጥያቄ በአግባቡ እየተመለሰ አይደለም፤ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ ለመፍታት ምን እየሠራ እንደኾነ ማብራሪያ እንፈልጋለን ነው ያሉት፡፡
👉 በሕዝብ ላይ እየደረሰ ያለው እገታና ሰላም ማጣትን መንግሥት እንዴት ለመፍታት እንዳሰበም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና የህወሃት ወቅታዊ የሰላም ቁርጠኝነት ምን እንደሚመስል ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል ተባለ፡፡
Next article“ስጋቶችን አጥበን፣ እድሎችን አስፍተን፣ እንደ ሀገር ጸንተን መኖር ይገባናል ” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)