
ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ምጣኔ ሀብታዊ ፈተና እና የኑሮ ውድነትን ማዕከል ያደረገው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 28ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተጀምሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2015 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም እና በ2016 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ ከምክር ቤት አባላቱ ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የምክር ቤት አባላቱ በዋናነት ምጣኔ ሀብታዊ እና የኑሮ ውድነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥያቄዎችን ቢያነሱም ለኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ ምክንያት የኾነው የውስጥ ሠላም እጦት እና የውጭ ግንኙነት ጥያቄዎች ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ውጫዊ ጫና እና ውስጣዊ ፈተና በበረታባት አሁናዊቷ ኢትዮጵያ መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ምን እየተሠራ እንደኾነ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጥያቄ ቀርቧል፡፡
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እና የቀይ ባሕር ፖለቲካ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያስችል የመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ወቅታዊ ግንኙነት ምን እንደሚመስል ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ፎረም አባል እንድትኾን ያለው ጥረት ምን ይመስላል ያሉት የምክር ቤቱ አባላት ከጎረቤት ሀገራት ሱዳን እና ኤርትራ ጋር ያለው ወቅታዊ ግንኙነት ምን እንደሚመስል ጠይቀዋል፡፡
ላለፉት ሦስት ዓመታት የዘለቀውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለማጠናቀቅ መንግሥት የወሰደው እርምጃ መልካም ጅምር ነው ያሉት የምክር ቤት አባላቱ የፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት እና የህወሃት ወቅታዊ የሰላም ቁርጠኝነት ምን እንደሚመስል ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። በተለይም ህወሃት አሁንም የትግራይን ወጣቶች ወደ ጦርነት ለማስገባት ሙከራዎችን እያደረገ ነው እየተባለ ይነሳል ያሉት የምክር ቤት አባል አሁናዊውን ዘላቂ የሰላም ሂደት ያለበትን ኹኔታ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁናዊ አፈጻጸም እና የሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ የድህነት ቅነሳ እና ተፈናቃዮችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ መንግሥት እየሠራቸው ያሉ ተግባራትን ማብራሪያ እንዲሰጣቸውም የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!