መቋጫ ያጡት የመንገድ ፕሮጀክቶች!

55

ባሕር ዳር: ሰኔ 29/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ጎንደር ዞን በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የሚሠሩ ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶች አሁንም መቋጫ አላገኙም። ከእነዚህ መንገዶች ውስጥ ከዳባት-አጅሬ፣ ከአጅሬ -ቅራቅር – ከተማ ንጉስ፣ ከበለስ- መካነ ብርሃን፣ ከደባርቅ – ቧሂት፣ ከቧሂት – ድልይብዛ፣ ከአዲ አርቃይ – ቡያ – ደጃች ሜዳ እና ከደባርቅ – ሊማሊሞ – ዛሪማ ተለዋጭ መንገዶች ይገኙበታል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከተጓተቱ ከስድስት ዓመት እስከ 11 ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአካባቢው ማኅበረሰብ የቅሬታ ምንጭ እንደኾኑ ቀጥለዋል፡፡ በጃናሞራ ወረዳ የመካነ ብርሃን ከተማ ነዋሪ እና የመንገድ ሥራውን በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩት አቶ ሞላ ዘውዱ ለአሚኮ እንደገለጹት በዞኑ ከሚሠሩት ፕሮጀክቶች አንዱ የኾነው የቧሂት መካነ ብርሃን መንገድ ከተጀመረ አስራ አራት ዓመት አስቆጥሯል፡፡

መንገዱ የአካባቢውን መልክዓ ምድር ባላገናዘበ እና ጥራቱን ባልጠበቀ መልኩ በመሠራቱ አስፋልቱ ፈርሷል፤ አፈር እና ድንጋዩ እየተናደም መንገዱን እየዘጋ ለተሸከርካሪ እያስቸገረ ይገኛል፡፡ ችግሩንም ለኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር በተደጋጋሚ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ 105 ኪሎ ሜትሮችን በማቆራረጥ ወደ ደባርቅ እንደሚጓዙ ነው አቶ ሞላ የነገሩን። እስከ 300 ብር እንደሚጠየቁም አንስተዋል፡፡ በበጋ ወቅት አልፎ አልፎ ከሚመደቡ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ውጭ በጭነት መኪና ከሸቀጥ ጋር ተጭነው እንደሚጓዙ ነግረውናል፡፡ በዚህም በተሸርካሪዎች ላይ በደረሰ አደጋ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡ የተጀመረው መንገድ ቢጠናቀቅ በ45 ኪሎ ሜትር አሁን ካለው እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡ መንገዱ ለጃናሞራ ወረዳ ብቻ ሳይኾን ለበየዳ፣ ለጠለምትና ሰሃላ ወረዳዎች አገልግሎት የሚሰጥ በመኾኑ የአካባቢው መልክዓ ምድር ታሳቢ ያደረገ የኮንክሪት አስፋልተ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን መንገድ መምሪያ ኀላፊ አቶ ወገኔ አማረ በዞኑ በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር የሚሠሩ ሰባት ፕሮጀክቶች ከስድስት እስከ 11 ዓመት መጓተታቸውን ነግረውናል፡፡ አስራ አንድ ዓመት ከተጓተቱት ውስጥ ደግሞ ከደባርቅ ቧሂት ድልይብዛ መንገድ ፕሮጀክት አንዱ እንደኾነ ነው ገለጹት፡፡ በኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር ጎንደር ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽኀፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ብሩክ አዳነ እንዳሉት የነዳጅ እና የስሚንቶ ችግር ፣ የፕሮጀክቶች አቅም ማነስ ፣ የጸጥታ ችግር ሥራውን በተገቢው መንገድ ለመሥራት ፈተና ኾነው ቆይተዋል፡፡ ከፕሮጀክቶቹ ውስጥ ሶስቱ በአንድ አቅጣጫ የሚሠሩት አዲስ በመኾናቸው ለመጓተቱ ሌላኛው ምክንያት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ የአቅም ችግር የነበረባቸውን ተቋራጮች በሌላ ተቋራጭ በመተካት የመንገድ ሥራው እንዲሠራ መደረጉን ገልጸዋል። አሁን ላይ ከሰባቱ መንገዶች ውስጥ አምስቱ በሥራ ላይ መኾናቸውንም ነው ያነሱት።

የደባርቅ ሊማሊሞ ዛሪማ ተለዋጭ መንገድ እና የአዲአርቃይ-ጠለምት የመንገድ ፕሮጀክቶች በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጠዋል፡፡ ቀሪ ሥራዎችን በሌላ ተቋራጭ ለማስጀመር የጨረታ ሰነድ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ በማኅበረሰቡ የሚነሳው የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ጥያቄ አካባቢው ካለው የቱሪስት ፍሰት አኳያ ተቀባይነት በማግኘቱ ለዋናው መስሪያ ቤት መቅረቡን አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ደጋግ ሕዝቦች መኾናችንን፣ ሰጪዎች እንጂ ተቀባዮች አለመኾናችን መግለጥ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleየፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና የህወሃት ወቅታዊ የሰላም ቁርጠኝነት ምን እንደሚመስል ማብራሪያ ሊሰጥ ይገባል ተባለ፡፡