የኋላ ሰሌዳቸዉ ተፈትቶ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር መበራከቱን አብመድ ታዝቧል፤ የሚመለከተው የፖሊስ ክፍል ደግሞ ድርጊቱ ወንጀል ስለሆነ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

230

ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 05/2012ዓ.ም (አብመድ) በተለያዩ አጋጣሚዎች መንገድ ዳር ቆሞ የተሽከርካሪዎችን ሕግ አክብሮ መንቀሳቀስ ለታዘበ ብዙ ችግሮችን መመልከት እንደሚችል እሙን ነው፡፡ ለአብነትም የኋላም ሆነ የፊት የተግባቦት መብራት (ፍሬቻ) የማይሠራ፣ ወደኋላ መመልከቻ መስታውት (ስፖኪዮ) የሌለው፣ የፊትም የኋላም ሰሌዳ የሌለው ወይም በከፊል የተቆረጠና ያልተሟላ ሰሌዳ ቁጥር ያለው፣ የፊት ለፊት ሰሌዳው ኖሮት የኋላ ሰሌዳ ቁጥር የሌለው ተሽከርካሪ መመልከት የተለመደ ነው፡፡

ለዛሬ ዘገባችን መነሻ የሆነን የሰሌዳ ቁጥር ጉዳይ ነው፤ የተሽከርካሪ የሰሌዳ ቁጥር አንድን ተሽከርካሪ ከሌሎች ተሸከርካሪዎች ለመለዬት የሚያስችል የመታወቂያ ቁጥር ማለት ነው፡፡ በሚንስትሮች ምክር ቤት የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/2009 መሠረት አንድ ተሽከርካሪ በሕዝብ ወይም በጭነት አገልግሎት ወይም ለግል ጥቅም ለመስጠት በመንዶች ለመንቀሳቀስ የሰሌዳ ቁጥር ከኋላና ከፊት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ካላሟላ በመንገዶች ላይ መንቀሳቀስ እንደሌለበትና አስፈላጊው የደንብ መተላለፍ ቅጣት እንደሚጣልበት ደንቡ ያስረዳል፡፡

አንድ አሽከርካሪ የመንጃ ፈቃድ ሳይዝ ወይም ጥፋት ባጠፋ ጊዜ የተሰጠውን የክስ ወረቀት ይዞ ድጋሚ ጥፋት አጥፍቶ የተገኘ እንደሆነ የተሽከርካሪው የፊትና የኋላ ሰሌዳ ተፈትቶ ተሽከርካሪዉ ይቆማል፤ አሽከርካሪዉ ተገቢውን ቅጣት ፈፅሞ ሲቀርብም ሰሌዳዉ ይሰጠዋል፡፡ ከዚህ አግባብ ውጭ ሰሌዳው የተፈታ ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡

ይሁን እንጅ በባሕር ዳር ከተማ መንገዶች ዳርቻ ቆመን እንደታዘብነው የተሽከርካሪዎቻቸውን የኋላ ሰሌዳ ፈትተዉ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡ ያነጋገርናቸው አሽከርካሪዎች ቅጣታቸውን አስፈጽመዉ እስኪመጡ ሰሌዳቸው በተቆጣጣሪዎች መፈታቱን ተናግረዋል፡፡ ያገኘናቸው ግን ቅጣት ለማስፈጸም እየሄዱ ወይም አስፈጽመው እየተመለሱ ሳይሆን አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

ስለጉዳዩ የጠየቅናቸዉ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመንገድ ትራፊክ ደኅንነት መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ የደንቡን ድንጋጌዎች ተላልፈው ሲገኙ የተሽከርካሪው የኋላ ሰሌዳ የመፍታት ልማዳዊ አሠራር ሲተገበር እንደነበር አስታውሰዋል፤ ድርጊቱ ለወንጀል መፈፀም የሚፈጥረውን ምቹ ሁኔታ ለመቀነስና የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብን በትክክል ለማስፈፀም በክልል ደረጃ በተላለፈ መመሪያ የተለምዶ አሠራሩ እንዲቀር መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

‹‹ማንኛውም በሕግ ስልጣን የተሰጠዉ ተቆጣጣሪ ድርጊቱን አይፈፅምም›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጅ የሚፈፅሙትን የደንብ መተላለፍ ድርጊት ከተቆጣጣሪዎች ዕይታና ክትትል ለመሰወርና ሌሎች የወንጀል ድርጊቶችን ለመፈፀም የኋላ ሰሌዳ ፈትተዉ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች እንዳሉ ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ አረጋግጠዋል፡፡ የተቆጣጣሪዎች ቸልተኝነት ለድርጊቱ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ የገለፁት ኃላፊዉ ድርጊቱን ለማስቆም ቁጥጥር እንደሚደረግና ድርጊቱን ፈፅመዉ በሚገኙት ላይም ከደንብ መተላለፍ ቅጣት ባለፈ ድርጊታቸው ለወንጀል ተግባር መዋል አለመዋሉን ለማረጋገጥ ምርመራ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

መንገደኞችስ የምንሳፈርበት መኪና የኋላና የፊት ሰሌዳው የተሟላ መሆኑን የማረጋገጥ ልምድ ይኖረን ይሆን? የኋላ ሰሌዳ የሌላቸው ተሽከርካሪዎች ጉዳት አድርሰውብን ቢያመልጡ ማን በምን ሊይዛቸው ይችላል? እስኪ ሐሳባችሁን አጋሩን?

ዘጋቢ፡- መሠረት ላቀ

Previous article“የዕርቀ ሠላም ኮሚሽኑ የተጣሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎችና እናውቅልሀለን ባዮች ያስታርቅ።” የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች
Next articleየግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ያለ ቀረጥ እንዲገቡ ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቅቋል፡፡