“ደጋግ ሕዝቦች መኾናችንን፣ ሰጪዎች እንጂ ተቀባዮች አለመኾናችን መግለጥ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

37

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አዲሱን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የሚዲያ ተቋም መርቀው ከፍተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዲሱ ሚዲያ ኮምፕሌክስ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያ ጥንታዊ ፣ ሰፊ የኾነ መሬት ያላት ፤ በሁሉም መመዘኛ ታላቅ ሀገር ናት ብለዋል፡፡ የሚሠሩ ተቋማት ታላቅነቷን የሚመጥኑ መኾን እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኢትዮጵያን እንዳገለገለውና እንደ እድሜው ልክ ያላደገ ተቋም መኾኑንም አንስተዋል፡፡

የሀገር ባለቤቶች እስከኾንን ድረስ የምንሠራቸው ተቋማት የእኛው ናቸው ብለዋል፡፡ ተቋማት እያስገነባን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአብነት መከላከያ በአፍሪካ ታላቅ የሚያደርገውን ተቋም ገንብቷል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ትልቁ ተቋም ኾኗል፣ ኢቲዮ ቴሌኮምም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አድጓል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነጻ ሳይወጡ የነበረ ተቋም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋሙን በሚመጥነው ልክ ቢደራጅ የኢትዮጵያን ታሪክ በአፍሪካ ደረጃ መገንባት ይችላል ነው ያሉት፡፡ ከሰፈር ወጥተን በአፍሪካ ደረጃ መታየት አለብን ነው ያሉት፡፡

ደጋግ ሕዝቦች መኾናችንን፣ ሰጪዎች እንጂ ተቀባዮች አለመኾናችን መግለጥ ይገባልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሊቪዥን ከእንግዲህ በኋላ በቴክኖሎጂ ማሳበብ አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ደረጃ ቦታዋን እንድትይዝ የሚያስችል መኾን አለበትም ብለዋል፡፡ ሳቢና ፈጣን መረጃዎችን ማቅረብ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ተቋማት ታላላቅ እየኾኑ እየተሠሩ መኾናቸውንም አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኢትዮጵያን በልኳ እንዲያስተዋውቅም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“አዲሱ የኢቢሲ ኮምፕሌክስ ግንባታ የኢትዮጵያን ልክ የምናሳይበት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
Next articleመቋጫ ያጡት የመንገድ ፕሮጀክቶች!