
ባሕር ዳር፡ ታኅሳስ 5/2012ዓ.ም (አብመድ) የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪዎች ከቀረጥ ነጻ እንደሚገቡ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ሀብቴ በተለይ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደገለጹት ‹‹የአገሪቱ ግብርና አልዘመነም›› የሚለውን ተደጋጋሚ ትችት ይቀርፋል፤ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎችን ዋጋ ከ50 እስከ 60 በመቶ የሚቀንስ ውሳኔም ነው፡፡ ከማሳ ዝግጅት እስከ መለስተኛ ምርት ማቀነባባር የሚያስችሉ 624 ዓይነት የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ናቸው ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ነው የተወሰነው፡፡
የምርት ብክነትን በእጅጉ ይቀንሳል፤ ከማሳ ዝግጅት እስከ መለስተኛ ምርት ማቀነባበር ሂደት የሚጠቅሙ የግብርና ሜካናይዜሽን መሳሪያዎች ናቸው ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የተወሰነው፡፡ ‹‹መንግሥት ይህንን ውሳኔ መወሰኑ ከግብር የሚያጣውን ገቢ ከተሻሻላ ግብርና ምርት ያካክሰዋል›› ብለዋል አቶ ታምሩ ሀብቴ፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከቀረጥ ነጻ የሚያደርገው መመሪያ ከውጭ የሚያስቡ አስመጪዎችን ብቻ ሳይሆን መለዋወጫ ከውጭ አስመጥተው ምርቱን በሀገር ውስጥ የሚገጣጥሙትንም ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡
በግርብርና ቴክኖሎጂው ላይ ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚ ማድረግ የግብርና ሂደቱን ከማዘመን ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል፣ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ያሻሽላል፣ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቴክኖሎጂዎቹ ‹‹የአርሶ አደሩን ኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴ በማዘመን ድካሙን በመቀነስ ምርታማ ያደርጉታል›› ተብሏል፡፡ ከቀረጥ ነጻ የሚደረገው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ብቻ ሳይሆን በሽያጭ ወቅትም እንደሆነ አቶ ታምሩ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በፊት ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ ብርቱ ቁጥጥር እና ክትትል ይደረጋልም ተብሏል፡፡
ዘጋቢ፡-የማነብርሃን ጌታቸው