“አዲሱ የኢቢሲ ኮምፕሌክስ ግንባታ የኢትዮጵያን ልክ የምናሳይበት ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

34

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዲሱ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተመርቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢቢሲ ከነጋሪት እስከ ኢንተርኔት በዘለቀው የመረጃ ሥርዓት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ነበረው ብለዋል፡፡

ባለፉት ክፍለ ዘመናት የዓለምን ገጽታ ከቀየሩ 10 የሚደርሱ የፈጠራ ሥራዎች መካከል ቢያንስ ሦስቱ ከሚዲያ ጋር ግንኙነት አላቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህትመት ማሽን ፈጠራ፣ የቴሌኮም ግኝት እና የኢንተርኔት መገኘት ሚዲያውን እንዲዘምን ብቻ ሳይኾን ተፅዕኖውም ላቅ ያለ እንዲኾን አድርገውታል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ እና መረጃ ግንኙነታቸው ጥብቅ እና የጥንት መኾኑን በማንሳት ከድንጋይ ላይ ጽሑፍ፣ ስዕል እና ሌሎች የግንኙነት አውታሮች ጋር ልምምድ ያላት ሀገር ናት ብለዋል፡፡ የብዙሃን መገናኛ ተቋማትን ተፅዕኖ ከኢትዮጵያዊያን በላይ የሚመሰክር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በመዝገበ ቃላት ላይ ሳይቀር በርሃብ እንድትገለጽ ተፅዕኖ የፈጠረው ሚዲያ ነበር ብለዋል፡፡

ኢቢሲ የተሳሳቱ ትርክቶችን በማረም፣ ትውልድ በመገንባት እና የሕዝብ ድምጽ በመኾን የጀመረውን የለውጥ ጉዞ ማስቀጠል ይገባል ተብሏል፡፡ የመንግሥት ልሳን እና የተለየ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች ድምጽ ማጉያ ሳይኾን ኢቢሲ ራሱን ችሎ የሚሰማ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም እንዲኾን ልትተጉ ይገባል ብለዋል፡፡

አዲሱ የኢቢሲ ኮምፕሌክስ ግንባታ የኢትዮጵያን ልክ የምናሳይበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተፈጥሮ ጋር ተገናኝታችኋል፤ ከሰፈር ጨዋታ እና አሉባልታ ወጥቶ ለተፈጥሮ እና ለሰው ልጅ የሚሠራ ተቋም ማድረግ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትለካው በተቋሞቿ ልክ በመኾኑ ሌሎች ተቋማትም ኢትዮጵያ የምትለካበትን የከፍታ ልክ እንዲያዘጋጁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጂቡቲ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋር አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
Next article“ደጋግ ሕዝቦች መኾናችንን፣ ሰጪዎች እንጂ ተቀባዮች አለመኾናችን መግለጥ ይገባል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)