
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ2015 በጀት ዓመት ሊቀርቡ ከታቀዱት 412 ትራክተሮች ውስጥ የ327 ትራክተሮች ግዥ መፈጸሙን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
ከ327 ትራክተሮች 175 የሚደርሱት ለአርሶ አደሮች መተላለፍ ችለዋል። የባንኮች አሠራር ለአርሶ አደሮች አለመመቸትና የትራክተሮች ዋጋ ከአርሶ አደሮች የመግዛት አቅም ጋር አለመመጣጠን
ተገዝተው የቀረቡ ማሽኖችን ወደ አርሶ አደሮች ለማሰራጨት እንዳላስቻለ ተነስቷል።
ቢሮው በእርሻ ሜካናይዜሽን አቅርቦት እና ስርጭት አፈጻጸም ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል። በውይይቱ ላይ የግብርና ባለሙያዎች፣ የዞን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ማሽን አቅራቢ ድርጅቶች እና የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል።
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ አቅርቦት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ የክልሉን የእርሻ ሜካናይዜሽን አቅርቦት እና ስርጭት ጥንካሬ እና ጉድለቶች በውይይቱ መክፈቻ ላይ አንስተዋል።
አበዳሪ ባንኮችን በማፈላለግ እና በማነጋገር እንዲሁም መነሻ በጀት በመመደብ በ20 | 80 አሠራር ትራክተሮችን ለአርሶ አደሮች ማከፋፈል መቻሉ እንደ ጥንካሬ ተነስቷል። ለትራክተር መግዣ የሚውለው ብድር የወለድ ምጣኔ ከ10 እስከ 11 ነጥብ 5 በመቶ እንዲኾን የተደረገው ጥረትም አበረታች ነበር ተብሏል።
ሁሉም ባይኾኑም አብዛኛዎቹ ትራክተር አቅራቢ ድርጅቶች ትራክተሮቹን በፍጥነት ገዝቶ ለማቅረብ ያሳዩት ቁርጠኝነትም እንደ ጥንካሬ ተነስቷል።
እንደጉድለት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ደግሞ ፦
👉እጅግ በተጓተተ ግዥ ምክንያት የተጠየቁ ማሽኖች እስካሁንም አልቀረቡም። በተለይም የግብርና ሜካናይዜሽን አቅራቢ ድርጅት ኮንባይነር ማቅረብ አለመቻሉ እና መቅረብ ከሚገባው ማሽን ውስጥ በጣም ዝቅተኛው ቁጥር ብቻ መቅረቡ በውስንነት ተገምግሟል።
👉 የአቅራቢ ድርጅቶች የመሸጫ ዋጋ ከፍተኛና የተለያየ መኾን አንዱ ምክንያት ነው። ለአብነትም የግብርና ሜካናይዜሽን አቅራቢ ድርጅት በአንድ ትራክተር ላይ ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ብር ጭማሪ መምጣቱ፣
👉ለማበደር ፈቃደኛ የኾኑ ባንኮች ጭምር ቢሮክራሲያቸው ለአርሶ አደሮች አለመመቸት፣
ዳይሬክተሯ እንደተናገሩት በ2015 በጀት ዓመት ለእርሻ ሜካናይዜሽን ማሽኖች ግዥ የሚውል 30 ሚሊዮን ዶላር ተመድቦ እንደነበር ተናግረዋል። ይህ በጀት 412 ትራክተሮችን፣ 5 ኮንባይነሮችን እና 5 ሺህ የውኃ መሳቢያ ፓንፖችን ለመግዛት ታልሞ የተበጀተ ነበር።
የታቀዱ 5 ሺህ የውኃ ፓንፖች ሙሉ በሙሉ የተገዙ ቢኾንም ወደ አርሶ አደሮች ግን አልተሰራጩም።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ተወካይ ተሳታፊ አቶ አንማው ገዳሙ አርሶ አደሩ ማልማት እንዲችል ልማት ባንክ የቻለውን ሁሉ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ባንኩ የትራክተሩን ሊብሬ ብቻ በመያዝ ከቢሮ ክራሲ የጸዳ የብድር አሰጣጥ እንደሚከተልም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኀላፊ አጀበ ስንሻው የእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ በዘመናዊ መልኩ መከናወን እንዲችል ባንኮች የሜካናይዜሽን ማሽኖችን ለሚገዙ አርሶ አደሮች ተገቢውን ብድር ማመቻቸት እንዳለባቸው ተናግረዋል። ብድር ባልተመቻቸበት ሁኔታ በአርሶ አደሮች አቅም ብቻ ማሽን ሊገዛ እና ግብርናው ዘምኖ ለሀገር ኢኮኖሚ ደጋፊ ሊኾን እንደማይችልም ገልጸዋል። ተገዝተው የቀረቡ ማሽኖች ወደ አርሶ አደሮች እጅ ገብተው የታለመለትን ግብ እንዲመቱ ለማስቻል የተቀላጠፈ አሠራር ማበጀት እንደሚያስፈልግም አቶ አጀበ ተናግረዋል።
አማራ ክልል ከአምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት ያለው ክልል ሲኾን ከዚህ ውስጥ 3 ሚሊዮን ሄክታሩ መሬት በትራክተር መታረስ የሚችል እና ለሌሎችም የሜካናይዜሽን ሥራዎች ምቹ ነው። በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋ እና አርሶ አደሮች ዘመናዊ የእርሻ ማሽኖች ባለቤት እንዲኾኑ መረባረብ እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ዘጋቢ፦ አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!