
ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ቀደመ ቦታው እንዲመለስ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት እየተካሄደ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ።
ውይይቱ የሶስቱም ክልሎች የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የትራንስፖርት ቢሮ አመራሮችን ያሳተፈ ነው።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ፥ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ከተቋጨ በኋላ መንግሥት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎች መልሰው እንዲቋቋሙ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ እንዲፀና እስከ ታች ያሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ውይይት ማካሄድ ይኖርባቸዋል፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማድረግም ይገባል ብለዋል አቶ ካይዳኪ።
የሶስቱ ክልሎች ሕዝቦች በትራንስፖርትና በሌሎች ጉዳዮች እንዲቀራረቡ መስራት ያስፈልጋልም ማለታቸውን ከሰላም ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!