የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አባላት በባንጃ ወረዳ የችግኝ ተከላ አካሄዱ፡፡

56

እንጂባራ: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል ሀሳብ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በባንጃ ወረዳ አርሳ ግምበኻ ቀበሌ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አባላት አካሂደዋል።

በመርሃ ግብሩ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኀይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) ጨምሮ የቢሮው ባለሙያዎች፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት አባላት እና ሌሎች ተጋቫዥ እንግዶችም ተገኝተው በባንጃ ወረዳ አርሳ ገምበኻ ቀበሌ ችግኝ ተክለዋል።

በችግኝ ተከላው ላይ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ኀይለማርያም ከፍያለው (ዶ.ር) እንደገለጹት በክልል ደረጃ ሰኔ 10/2015 ዓ.ም ጀምሮ የሁለተኛ ዙር የአረንጓዴ መርሃ ግብር “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ መልዕክት ተጀምሮ እስከ አሁን የተከላ መረሃ ግብሩ በክልሉ አካባቢዎች እየተካሄደ ነው።

1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ ለተከላ ተዘጋጅቷል ያሉት ቢሮ ኀላፊው የአዊ ብሄረሰብ አሥተዳደርም በችግኝ ተከላ ለሌሎች ተሞክሮ መኾን የሚችል በመኾኑ በዘንድሮ ክረምት እስከ 90 ሚሊዮን ችግኝ እንዲተክል ታሰቧል ብለዋል።
ኅብረተሰቡም የተተከሉ ችግኞችን በባለቤትነት ተንከባክቦ አጽድቆ ለተሞክሮ እንዲበቁ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በባንጃ ወረዳ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአዊ ብሄረሰብ አሥተዳደር አሥተዳዳሪ እንግዳ ዳኛው ተገኝተው ችግኝ የተከሉ ሲኾን የአዊ ሕዝብ ለደን ልማት ያለው አመለካከት ከፍተኛ በመኾኑ አብዛኛው አካባቢዎች በደን ተሸፍነዋል ብለዋል።

የአዊ ሕዝብ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይኾን ተንከባክቦ ለውጤት በማድረስ የቆየ ልምድ ባለቤት እንደኾነ የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው፤ ዛሬ የተተከለውን ችግኝ የእንክብካቤ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ደረጃ ሰኔ 16/2015 ዓ.ም ጀምሮ ከ300 ሺህ በላይ ችግኞችን መትከል መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የአዊ ብሄረሰብ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ኀላፊ ታደሰ አስፋው (ዶ.ር) ናቸው።

በወል መሬቶች፣ በተቋማት እና በበጋ ወራት ተፋሰስ በተሠራባቸው ቦታዎች ከ80 ሚሊዮን በላይ የደን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀቱን ነው መምሪያ ኀላፊው የገለጹት።

በዛሬው የተከላ ፕሮግራም ከ10 ሺህ በላይ የደን ችግኞች በቀበሌው ተተክለዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ስንታየሁ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 27ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ማካሄድ ጀመረ።
Next articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo, Waxabajjii 30/2015