
እንጅባራ: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ስልጣንና ተግባር መሠረት የብሔረሰብ አሥተዳደሩን እቅድ አፈፃፀም ከመከታተል ባለፈ የመቆጣጠር፣ የመገምገም እና አቅጣጫ የማስቀመጥ ሥራዎችን በማከናወን ኅብረተሰቡን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሙሉአዳም እጅጉ ተናግረዋል።
አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ፣ ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ሕገ ወጥነትና መሬቶችን ለመውረር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መቆም አለባቸው ያሉት አፈ ጉባዔዋ የምክር ቤቱ አባላት መሰል ድርጊቶችን አምርረው በመታገል ኀላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።
አሁን ላይ ዜጎችን እያማረረ የሚገኘውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ በበጋ መስኖ የተመዘገበውን መልካም ውጤት በክረምት የሰብል ሥራዎችም መድገም እንደሚገባ አንስተዋል።
ከመኸር ሰብል ልማት ጎን ለጎን አረንጓዴ ልማት፣ የክረምት የወጣቶች በጎ ፍቃድ ተግባርን አቀናጅቶ መፈጸም ይገባል ያሉት አፈ ጉባዔዋ ይህንን ሥራ ሁሉም የምክር ቤት አባላት ቁልፍ ተግባር እና አጀንዳ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው ጉባዔው የተመረጡ ሦስት ተቋማት የአስፈፃሚ እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የሚካሄድ ሲኾን ምክር ቤቱ የተቋማት ኀላፊዎችን ሹመት ማጽደቅ እና የተለያዩ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
ዘጋቢ፦ሰለሞን ስንታየሁ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!