አዲሱ ክልል” የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” በሚል ስያሜ እንዲዳራጅ ተወሰነ።

109

ባሕር ዳር: ሰኔ 28/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውስጥ በስድስት ዘኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ የጌዴኦ ፣ የወላይታ ፣ የጋሞ ፣ የጎፋ ፣ የኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዘኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የኧሌ ልዩ ወረዳዎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሚል ስያሜ እንዲዳራጅ ተወስኗል።

የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ፣ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን ባካሄደበት በዛሬው ቀጣይ ዉሎው የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተካተቱበት «የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል» በሚል ስያሜ አዲስ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ቀድሞ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ይኖሩ የነበሩ የስድስት ዞኖችና የአምስት ልዩ ወረዳዎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባካሄዱት ሕዝበ ውሳኔ በአንድ ክልል የመደራጀት ፍላጎታቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን ውሳኔ መሰረት በማድረግ በአንድ ክልል እንዲደራጁ በዛሬው እለት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ወስኗል፡፡

«የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል» በሚል በአዲስ የተደራጁት በወላይታ፣ በጋሞ፣ በጎፋ፣ በጌዲዮ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በኮንሶ ዞኖችና በደራሼ፣ በቡርጂ፣ በአማሮ፣ በኧሌና በባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው፡፡

ቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል ውስጥ የነበሩ የሀድያ፣ የሀላባ፣ የከምባታ ጠምበሮ፣ የስልጤ፣ የጉራጌ ዞኖችና የየም ልዩ ወረዳ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነባሩ የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በነባሩ ክልል የሚቀጥሉ ይሆናል።

እንደ ምክር ቤቱ መረጃ፤ የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛው የፓርላማ ዘመን፣ በ1ኛ ዓመት የሥራ ጊዜው ነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ውስጥ በስድስት ዘኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ የጌዴኦ ፣ የወላይታ ፣ የጋሞ ፣ የጎፋ ፣ የኮንሶ እና የደቡብ ኦሞ ዘኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የኧሌ ልዩ ወረዳዎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ ክልል ለመመስረት ያቀረቡትን ጥያቄ በመቀበል በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 47/3/(ለ)መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጂ እና በጋራ ክልል የመመሥረት ጥያቄው የሕዝቡን ይሁንታ ስለማግኘቱ የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት ሪፖርት ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መምራቱ ይታወሳል::

አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር የውሳኔ ሀሳቡ እንዲጸድቅ ለድምጽ አቅርበው ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ደግፎ አጽድቆታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ለሀገር አቀፍ ፈተና ወደ መፈተኛ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሄዱ የአካባቢያቸው አምባሳደር መኾን አለባቸው” የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ
Next articleየአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 27ኛ መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ማካሄድ ጀመረ።